የከተማ አስተዳደሩ በግንባታው ዘርፍ እያደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል ጥራት ያላቸው ግንባታዎችን ለማከናወን አግዞናል-የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ አስተዳደሩ በግንባታው ዘርፍ እያደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል ጥራት ያላቸው ግንባታዎችን ለማከናወን አግዞናል-የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2017 (ኢዜአ):-የከተማ አስተዳደሩ የግንባታ ፍቃድን ጨምሮ በዘርፉ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እና ክትትል ግንባታቸውን በጥራት ለማከናወን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያዎች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የህንጻና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና እድሳቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በመዲናዋ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያዎች መካከል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት አካባቢ የሚገኘው ቴምር ፕሮፐርቲስ ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር ብርሃኑ ኢያሱ በከተማው የሚገነቡ ህንጻዎች የከተማውን ውበትና የጥራት ደረጃ የጠበቁ መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የዲ.ኤ ኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ኢንጂነር አለምነህ ፍቃደ እና ኢንጂነር ቶማስ ሰለሞን በበኩላቸው ደረጃቸውን ያልጠበቁ ግንባታዎች ለደህንነትም ስጋት ከመሆናቸውም ባለፈ የኢኮኖሚ ኪሳራ የሚያስከትሉና ገጽታም ጭምር የሚያበላሹ ናቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዛሬ የሚነገቡ ግንባታዎች ለመጪው ትውልድ ጭምር የሚጠቅሙ እና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ በሚገነቡት ግንባታዎች ጥራት፣ ደህንነትና ደረጃ ማስጠበቅ ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የግንባታ ፍቃድን ጨምሮ በዘርፉ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ክትትል ግንባታቸውን በጥራት ለማከናወን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ በከተማዋ ደረጃቸውን የጠበቁ ግንባታዎችና እድሳቶች እንዲከናወኑ የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በከተማው ውስጥ የሚዘረጉ የውሃ፣ መብራት፣ ቴሌ፣መንገድ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተቀናጅተው እንዲሰሩና የሃብት ብክነት እንዳይኖር የማስተባበር ስራ ይሰራል፡፡
በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት በግንባታ ስራ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉና ተገቢውን መስፈርት ላሟሉ የግንባታ ስራ ተቋራጮች ፈቃድ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ 11 ሺህ በላይ አዲስ ህንጻዎችና ከ 12 ሺህ በላይ ነባር ህንጻዎች ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸውን በተመለከተ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አዲስ ህንጻዎች የግንባታ ከ 41 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነባር ህንጻዎች የእድሳትና ጊዜያዊ የግንባታ ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል ስራዎችም ከህንጻ አዋጁ መመሪያ ውጭ ግንባታ ሲያከናውኑ የተገኙ መኖራቸውን አንስተው በእነዚህ አካላት ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከህገ ወጥ ግንባታን ጨምሮ በሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት ላይ በተላለፈ የቅጣት ውሳኔ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።