ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫና የውስጥ አቅምን በተግባር ያየንበት ታሪካዊ ዓርማችን ነው

ጋምቤላ፤ነሐሴ 24/ 2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫና የውስጥ አቅምን በተግባር  ያየንበት ታሪካዊ  ዓርማችን  ነው ሲሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን በአንድነት ያስቀመጡበት ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

‎ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ፔን ኡጁሉ፤  ታላቁ የኢትዮጵያ  ሕዳሴ ግድብ የሕብር ብሔራዊ አንድነት መገለጫና የይቻላል መንፈስን የፈጠረ  ነው ብለዋል።


 

ግድቡ ኢትዮጵያዊውን በአንድነት ከተባበሩ ያሰቡትን ሁሉ በድል አድራጊነት መሸጋገር የሚችሉ መሆኑን ያመላከተ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ፍፃሜ ላይ የደረሰው ይኸው የሕዳሴ ግድብ  ከኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ባለፈ በሀገሪቱ እየተካሄዱ ለሚገኙ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የግብርናና ሌሎች የብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።-

ጀግኖች አባቶች በአንድነት በአድዋ ያሳዩን የአይበገሬነትና የአሸናፊነት ታሪክን በሕዳሴው ግድብ ግንባታ የዘመኑ ትውልድ ደግሞታል  ያሉት ደግሞ ሌላው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ አንዳርጌ ዋሲሁን ናቸው።


 

በሕዳሴው ግድብ ግንባታ የታየው ትብብርና አንድነት በራስ አቅም ሌሎች ፕሮጀክቶችን መከወን እንደሚቻል ትምሕርት የሰጠ ነው ብለዋል።

ሕዝቦች ሕብረታቸውን አጠናክረው በጋራ ከሰሩ የማያሳኩት ልማትና የማይሻገሩት  እንደሌለ የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ለዘመኑ ትውልድ ትልቅ ተሞክሮ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ኮንግ ጋድቤል በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት አሻራቸውን ያስቀመጡበት  ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሕዝቦች አንድነትና ትብብር በግድቡ ዙሪያ የነበሩ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ የግድቡን ግንባታ እውን ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም