ቀጥታ፡

የሀገር ውስጥ ምርትን መግዛት ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያሳልጥ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 24/ 2017 (ኢዜአ)፦የሀገር ውስጥ ምርትን መግዛት ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያሳልጥ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጥራት መንደር የተዘጋጀውን "የኢትዮጵያን ይግዙ" ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽንና ባዛር ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።'


 

በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ዕውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር ተከናውኗል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በመርሀ ግብሩ ላይ በሰጡት የሥራ መመሪያ፤የሀገር ውስጥ ምርት መግዛትና መጠቀም የሀገራዊ ኢኮኖሚን የሚያደረጅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ምርት ይግዙ ስንል የሀገር ውስጥ ምርቶችን ጥራት ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ድርሻ አሳድጉ ማለት ነው ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርት ጥራትና ፍጥነት የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ለጤናማ ኢኮኖሚ መሰረት በመጣል መልካም የዕድገት ተስፋ ይሰጣል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ኤክስፖ የሀገር ውስጥ አምራችና ሸማቾችን በማገናኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዕድገት ምዕራፍ ላይ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ኢትዮጵያ በሀገራዊ ሪፎርሙ ታግዛ አበረታች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያስመዘገበችው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ያረጋገጡት ለውጥ መሆኑን በመግለፅ፣ በዚህም የወጭ ንግድ ጨምሯል የዋጋ ግሽበት በእጅጉ ቀንሷል ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በፍጥነት ገቢራዊ በማድረግና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ የሚዘልቁበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ ገቢ ምርትን መጠቀም ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዓለም የኢኮኖሚ ስርዓት በሚቀየርበት ወቅት ወሳኝ ይሆናል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ሀገራዊ ሀብትን በማባዛትና በማደራጀት የጎላ ትሩፋት ይኖረዋል ነው ያሉት።

የሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት በመጨመር የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ያደረጃል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ቢዝነስ የመፍጠር ክህሎትን ያሳድጋል፣ በራስ ባህል፣ ወግና በራስ ጸጋ መኩራትን እንደሚያላብስ ገልጸዋል።

በመሆኑም አምራቾች የምርት ጥራትና ፍጥነትን በማሳደግ የገበያ ደርሻቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ በማቅረብ፣ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሸማቾች የሀገር ውስጥ ምርት ሲገዙ የሀገራቸውን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ለወገናቸው የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን እንዲረዱም አሳስበዋል።

ባለሀብቶችና የፋይናንስ ተቋማት ከሀገር ውስጥ ባሻገር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚሳተፋ አምራቾችን ለማፍራት በፋይናንስ ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።

የንግድ ስርዓቱን ማዘመን እና ኢኮኖሚን መገንባት ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ግን ጅምሩ ሞገስ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም