ቀጥታ፡

አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ነው

ቦንጋ፤ ነሐሴ 24/2017 (ኢዜአ)፦ አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው አመለከቱ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አዲሱን የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቅ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

አቶ ማስረሻ በመድረኩ ንግግር ሲያደርጉ እንደገለፁት፤ በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ወሳኝ ነው።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ጥሬ ዕቃ በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት ለማምረት የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

እንዲሁም ተኪና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግና በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

የግብርናው ዘርፍ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የሀገር ኢኮኖሚን ለማሻገር ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑንም አቶ ማስረሻ አንስተዋል።

ፖሊሲው ከሀገራዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ መሻሻሉን ጠቅሰው፣ በየዘርፉ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከአዲሱ ፖሊሲ ጋር የተቃኘ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

መድረኩ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ፖሊሲውን በተገቢው በመረዳትና ወጥ ግንዛቤ በመያዝ ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ፖሊሲና የምግብ ሥረዓት ዳይሬክተር አቶ ረታ ዋቅጋሪ ፖሊሲው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለሀገራዊ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።


 

ግብርናን በማዘመን ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለወጪ ንግድ በቂ ምርት ማቅረብ የተቀመጡ የፖሊሲው ዓላማዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃን በማሻሻል ዘላቂ አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ ሀገራዊ የደን ውጤት ፍላጎትን ለማሟላት፣ የአደጋ  ተጋላጭነትን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር በፖሊሲው  የተካተተ ዓላማ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመድረኩም የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር)፣ የደንና አካባቢ ልማት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዳመነ ዳሮታና ሌሎች አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የክልል ካቢኔ አባላትና የዞን ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም