ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ተደራሽነት አጀንዳን በስፋት ታንጸባርቃለች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 24/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ ንብረት ጉባኤ ላይ የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ የማግኘት አጀንዳን አጉልታ እንደምታሰማ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ ያዘጋጁት ነው።

ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።

በጉባኤው ላይ ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ ልዑካን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ከግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን የጉባኤውን ዝግጅት በማስመልከት ለጋዜጠኞች ያዘጋጀው የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን፥ ኢትዮጵያ በቅርቡ ሁለት ትላልቅ ሁነቶችን እንደምስታናግድ ገልጸዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና የአፍሪካ አየር ንብረት ሳምንት እንደሚከናወን አመልክተዋል።

የአየር ንብረት ሳምንቱ ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ጉባኤው የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች እና የተግባር ምላሾች ጎልተው የሚታዩበት እንደሆነ ተናግረዋል።

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽና የገንዘብ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ምንጭ የሆነች አህጉር መሆኗን የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያላትን የመሪነት ሚና በመወጣት የትርክት ለውጥ እንዲመጣ ትሰራለች ብለዋል።

በካይ ሀገራት የገቡትን የፋይናንስ ቃል ኪዳን ተፈጻሚነት ጉዳይ ላይ ድምጿን በማሰማት

የአፍሪካን የፍትሐዊነት ጥያቄ እንደምታቀርብ ነው የተናገሩት።

ከጉባኤው በኋላ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ የአዲስ አበባ ድንጋጌ ይፋ እንደሚደረግና ለተፈጻሚነቱ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

እስከ አሁን ባለው መረጃ መሪዎችን ሳይጨምር 21 ሺህ 600 በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ መመዝገባቸውን ነው የጠቆሙት።

በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ መሰረት እንደሚጥል ተናግረዋል።

ጋዜጠኞች በሁነቶቹ ላይ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ውጤታማ ዘገባ እንዲሰሩ ለማድረግ ስልጠናው መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአፍሪካ መልካም ገጽታን እና የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ማጉላት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

መሪዎች የገቧቸው የአየር ንብረት ለውጥ ቃልኪዳኖች ትግበራ ተጠያቂነት እና የአዲስ አበባ ድንጋጌ ተፈጻሚነትና አተገባበር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአየር ንብረት የሳይንስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሰው፣ የልማት እና የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በዚህ ረገድም ጋዜጠኞች ጉዳዩን በውል ተረድተው ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በስልጠናው ላይ ሁለተኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ዝግጅት አስመልክቶ የተዘጋጁ ጽሁፎች ቀርበው ውይይቶች ተደርገዋል።

በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያና አፍሪካ ህብረት የጋራ ጥምረት 51 ሁነቶች የሚካሄዱ ሲሆን የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያዘጋጇቸው 186 ሁነቶች ተዘጋጅተዋል።

24 መካነ ርዕዮች (ፓቪሊዮኖች) ተዘጋጅተው የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ መካከል ስራዎች አውደ ርዕዮች ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም