የሻይ ቅጠል ምርትን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወሳኝ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለማድረግ በዘርፉ ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሻይ ቅጠል ምርትን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወሳኝ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለማድረግ በዘርፉ ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዳማ ፤ነሐሴ 24/2017(ኢዜአ)፦ የሻይ ቅጠል ምርትን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወሳኝ የሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለማድረግ በዘርፉ ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ከለውጡ በፊት ለሻይ ቅጠል ልማት የተሰጠ ትኩረት አናሳ መሆኑን ገልፀዋል።
ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለዘርፉ ልማትና እድገት ትኩረት መስጠቱን የገለጹት አቶ ታጋይ በዚህም የሻይ ልማት ኢንሼቲቭ ተቀርፆ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሻይ ልማት ኢንሼቲቭ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም አምናና ዘንድሮን ጨምሮ ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሻይ ልማት መሸፈኑን አብራርተዋል።
በተወሰነ ደረጃ ውሽውሽና ጉመሮ ሻይ በግሉ ዘርፍ ኤክስፖርት እየተደረጉ ቢሆንም ካለው አነስተኛ የሻይ ልማት አኳያ ምርቱ በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ እየዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሀገራችን ለሻይ ልማት የሚሆን ከፍተኛ እምቅ አቅም አለ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ በአሲዳማነት የተጠቁና ምርታማነታቸው ከ50 በመቶ በላይ የቀነሱ መሬቶች ለሻይ ልማት አመቺ ናቸው ብለዋል።
ለዚህም ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው በጥናቱ ቦታዎችን የመለየትና ምርጥ ዘር የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በዚህም የሻይ ልማቱን ከሁለቱ ክልሎች ባሻገር በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የጉራጌ ተራራማ አካባቢዎች፣ በአማራና ሌሎች ክልሎችም ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በደጋማው አካባቢ የሚለማው የሻይ ቅጠል በዓለም ገበያ ተፈላጊ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሀገራችን ደጋማ አካባቢዎች ልማቱን ለማስፋፋት ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሻይ ልማት ምንም ወጪ ሳይፈልግ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም ባለፈ ከኤክስፖርት ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ድርሻው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የተተከለው የሻይ ቅጠል በቀጣይ ዓመት ምርት መስጠት ይጀምራል ያሉት አቶ ታጋይ ምርቱን በጥራት ለማምረትና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
ለዚህም የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው በተያዘው በጀት ዓመትም ሰባት የሻይ ቅጠል ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታትም ሻይ ቅጠል ከቡና ቀጥሎ ለሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ዘርፍ እንዲሆን ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ ታጋይ አስረድተዋል።