የበካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂ ምቹና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር ያስችላል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 24/2017(ኢዜአ)፦በካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂ በተሽከርካሪዎች ላይ መገጠሙ ምቹና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር እንደሚያስችል የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያ ከ2018 ዓ.ም መስከረም ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

የበካይ ጋዝ ልቀት መመሪያ ቁጥር 1051/2017 ተግባራዊ ሲሆን፤ የአየር ብክለትን ከመቀነስ እና የነዳጅ አጠቃቀምን ከማሻሻል ባሻገር በተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት ሳቢያ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ያግዛል። 


 

መመሪያው ተሽከርካሪዎች የጋዝ ልቀታቸውን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ በመግጠም የአየር ብክለት እንዲቀንስ የማድረግ ዓላማ ይዟል። 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሀሰን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከተሽከርካሪ የሚወጣን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች።

ከእነዚህ መካከል የነዳጅ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ በማገድ በምትካቸው የአየር ብክለት የማያስከትሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተሰራውን ስራ ለአብነት አንስተዋል፡፡


 

መመሪያው የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ደረጃን ያላሟሉ ተሽከርካሪዎች ልቀቱን ለመቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ግዴታን የሚያስቀምጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ታልሞ የተዘጋጀው መመሪያው ከ2018 ዓ.ም መስከረም ጀምሮ በመላ አገሪቷ በሚገኙ ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ተሽከርካሪዎች የተቀመጠውን ደረጃ ካላሟሉ የበካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂውን መግጠም እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀው፤ የጭስ ልቀትንና የነዳጅ አጠቃቀምን የሚያስተካክሉ ቴክኖሎጂዎች በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መመሪያው ከተሽከርካሪዎች  የሚወጣው የበካይ ጋዝ ልቀት በጤና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን የሙቀት አማቂና በካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም