የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ የ"አረቅጥ " ሀይቅን ከጉዳት በመታደግ ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ የ"አረቅጥ " ሀይቅን ከጉዳት በመታደግ ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ወልቂጤ ፤ነሐሴ 24/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ሲከናወን የቆየው የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ የ "አረቅጥ" ሀይቅን ከጉዳት በመታደግ ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።
የ"አረቅጥ" ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሰብስቤ ተካ እንዳመለከቱት፤ በከተማው አቅራቢያ የሚገኘው የ"አረቅጥ" ሀይቅ በዙሪያው ባጋጠመው የአፈር መሸርሸርና የደለል ጉዳት ሊደርቅ ተቃርቦ ነበር።
ሀይቁን ለመታደግም በተፋሰስ የማልማትና ወደ ሀይቁ የሚገባውን ደለል የመከላከል ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በተለይም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከማልማት ባለፈ በአቅራቢያው የነበሩ ባህር ዛፍን ጨምሮ ሌሎችም ውሃ የመምጠጥ እና የመሬት ለምነት የሚያሳጡ ተክሎች የማንሳትና የእርከን ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ነው ያወሱት።
በዚህም በአጠቃላይ ከ25 ሄክታር በላይ የሚሸፍን በሀይቁ ዙሪያ ተጎድተው የነበሩ አካባቢዎች እንዲያገግሙ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎም ሀይቁ መልሶ ማገገሙን አንስተው፤ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ተፈጥሮን መመለስና ውብ አካባቢ ማድረግ እንደሚቻል ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ሀይቁ ለ"አረቅጥ " ከተማ ተጨማሪ ውበት ወደመሆን መድረሱን ያነሱት አቶ ሰብስቤ፤ ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ አካባቢ በመሆን በርካቶች የሚዝናኑበትና የስራ ዕድል መፍጠሪያ መሆን መቻሉን አስረድተዋል።
5 ማህበራት በዓሳ ማስገር እና በመዝናኛ ጀልባ አቅርቦት መሰማራታቸውን እና ለበርካቶች የስራ ዕድል ማስገኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀይቁ የዓሳ ምርትና የመዝናኛ አገልግሎት የማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዓሣ ሀብት ተመራማሪ ይርጋ እናውጋው (ዶ/ር) ፤ አካባቢን በአግባቡ ማልማትና ተፈጥሮን መጠበቅ የውሃ አቅምን ለመጨመር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ ይዘቱ እየተመለሰ ያለው የ"አረቅጥ" ሀይቅ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎችና መጠን እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ሀይቁን ለኢኮ ቱሪዝም ልማት በማዋል ገቢ ማመንጨትና ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ መደረጉን ተናግረዋል።