ጤናማ አመጋገብ እንዴት ያለ ነው? - ኢዜአ አማርኛ
ጤናማ አመጋገብ እንዴት ያለ ነው?
ህመምን ለመከላከል ከሚመከሩት ወሳኝ ተግባራት መካከል አንዱ ጤናማ አመጋገብ እንደሆነ ይነሳል።
ለመሆኑ ጤናማ አመጋገብ ሲባል ምን ማለት ነው?
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ትርጓሜ፤ ጤናማ ምግብ ማለት ሁሉንም የሥርዓተ ምግብ መጓደል ችግሮች ማለትም (የማይክሮኒዩትሬንት እጥረት፣ ከመጠን በታች መመገብ፣ ከመጠን በላይ ክብደት እና ከመጠን በላይ ውፍረት) እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የአመጋገብ ዘይቤ ነው።
በፈረንጆቹ 2024 የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት እና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጡት መመሪያ መሠረት ጤናማ ምግብ አራት መሠረታዊ መርሆዎችን መያዙን በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥርዓተ-ምግብ፣ የአካባቢ ጤናና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ ዳዊት ዓለማየሁ ይገልጻሉ።
እነዚህ መሠረታዊ መርሆዎችም፤ በቂ መሆን (Adequacy)፣ ሚዛንን መጠበቅ (Balanced)፣ ልከኝነት (Moderation) እና የተሰባጠረ (Diversity) መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
በቂ መሆን፦ ሁሉንም አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች እና እነሱን የያዙ የምግብ መደቦች በበቂ መጠን እንዲሁም ከፍላጎት በላይ ሳይሆን ማቅረብ ማለት ነው ይላሉ።
በዚህም የአመጋገብ ፍላጎቶችን ከዕድሜ፣ ጾታ፣ የእንቅስቃሴ ደረጃ እና የፊዚዮሎጂ ሁኔታ ጋር ማመጣጠን አስፈላጊ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
ሚዛንን መጠበቅ፡- ማክሮኒዩትሬንቶች (ፕሮቲን፣ ስብ እና ካርቦሃይድሬት) እድገት፣ ጉልበት እና አጠቃላይ ጤናን በሚደግፉ መጠን መወሰድ አለባቸው ማለት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ልከኝነት፡- ከጤና አደጋዎች ጋር የተገናኙ ንጥረ ነገሮች እንደ ስኳር፣ ሶዲየም (ጨው)፣ የሳቹሬትድ ፋት (ጠጣር ስብ) እና ትራንስ ፋት (ተፈጥሯዊ ባሕርይው በፋብሪካ የተቀየረ ስብ)፣ በተጠበቀ ገደብ ውስጥ መጠበቅ አለበት ማለት ነው፤ ይህም ለህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ስብጥር፡- እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን በተመጣጠነ ሁኔታ ማካተት በቂ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት ከማስቻሉም በላይ፤ የምግብ እጥረትን ለመከላከል ይረዳል።
በተጨማሪም ጤናማ ምግብ ደኅንነነቱ የተጠበቀ መሆን እንደሚገባው ነው የሚናገሩት።
የተሰባጠረ አመጋገብ ማለት በአንድ ገበታ በአንድ ጊዜ ቢያንስ አራት የምግብ ምድብ እንዲሁም በቀን ስድስት የተለያየ የምግብ ምድብ የያዘ ማለት ነው ይላሉ ባለሙያው።
የተሰባጠረ ምግብ ለጤና ተስማሚ መሆኑን በመገንዘብ፤ በተቻለ መጠን የሚፈለገውን ንጥረ-ምግብ ማሟላት ለጤናማ አኗኗር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም መክረዋል።
የኢትዮጵያ ምግብን-መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ስድስት የምግብ መደቦችን መያዙን ጠቅሰው፤ እህልና ሥራሥር (እንጀራ፣ ዳቦ፣ ቆጮ እና ቆሎ)፣ ጥራጥሬ (አተር፣ ምስር ሽምብራ እና ባቄላ)፣ለውዝ እና የቅባት እህል (ለውዝ፣ ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ሱፍ፣ ተልባ)፣ የእንሰሳት ተዋፅዖ (የዶሮ፣ የከብት፣ የፍየል፣ የበግ ሥጋ እና ዓሣ፣ ዓይብ፣ እርጎ)፣ አትክልትና ፍራፍሬ (እንደ ወጥ ወይም ሰላጣ የሚዘጋጁ አትክልቶች፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶና ሌሎች ፍራፍሬዎች) እንዲሁም ቅቤ እና ዘይት መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ውኃ ከስድስቱ የምግብ ቡድኖች የማይካተት ቢሆንም ለጤና በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኑሮ ሁኔታ እና አቅም በፈቀደ መጠን አመጋገብን ጤናማ በማድረግ ቀድሞ በበሽታ የመያዝ እድልን መቀነስ እንደሚቻል መክረዋል።