የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የሚለካ ውጤት እንዲያስመዘግብ አባል ሀገራት ድጋፍ ማድረግ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የሚለካ ውጤት እንዲያስመዘግብ አባል ሀገራት ድጋፍ ማድረግ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የሚለካ ውጤት እንዲያስመዘግብ አባል ሀገራት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው የገንዘብ ሚኒስትር እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች፣ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ፎረም እያስተናገደች ነው።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
የገንዘብ ሚኒስትር እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መድረኩ ለሁሉም አባል አገሮችና ለቀጣናው ጠቃሚ ነው።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ማጭበርበርን እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ለሁሉም ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን መከላከል የቀጣናውን ደህንነት በማረጋገጥ አስተማማኝ ኢንቨስትመንት መሳብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ማዕቀፍ ብዙ አገሮች ጥሩ እየሰሩ ቢሆንም ውስንነት ያለባቸውም እንዳሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የቡድኑን ራዕይ ለማሳካት የህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር የወንጀል ሰንሰለቱን መበጠስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የሚለካ ውጤታማነት እንዲያስመዘግብ በአንድነታችን ላይ ቁርጠኛ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ቀጣናዊ አንድነትን በማጠናከርና ትብብር በመፍጠር የተጠናከረ ቀጣናዊ ግንባር እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የግሉንና የመንግስትን ትብብር በማሳደግ ቀጣናዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ራዕይ እንዲሳካ በጋራ የመስራትና የመተባበር ስራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ዘመኑ የፈጠራቸው ቴክኖሎጂ መር የፋይናንስ ስርዓት /ፊንቴክስ እና በተለያዩ የፋይናንስ ዘርፉች /DNF አማካኝነት በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል እንዳይከሰት በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡