ጉባኤው የኢትዮጵያን ማንሰራራት እና የብልጽግና ጉዞ ለማሳወቅ ምቹ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው የኢትዮጵያን ማንሰራራት እና የብልጽግና ጉዞ ለማሳወቅ ምቹ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ 41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ የኢትዮጵያን የማንሰራራት እና የብልጽግና ጉዞ ከአፍሪካና ሌሎች አህጉራት ለመጡ ተሳታፊዎች ለማሳወቅ ምቹ ዕድል መፍጠሩ ተገለጸ፡፡
"የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
42ኛውን የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ የምስራቅ አፍሪካዋ አገር ታንዛኒያ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።
ጉባኤው አባል አገሮች ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው የትምህርት ምዘና ስርዓት መገንባት የሚያስችላቸውን ልምድ ያገኙበት መሆኑም ተጠቁሟል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቷን ለማሻሻል ያከናወነቻቸው ተግባራት ለውጥ ማስገኘት ጀምረዋል።
አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በመተግበር ብሎም አዳዲስ አሰራሮችን ስራ ላይ በማዋል ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ መዋዕለ ህጻናት መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
የጾታ አኩልነትን በማረጋገጥ፣ የአካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ትምህርትን በማረጋገጥ ሁለንተናዊ የትምህርት ተደራሽነት ማሳካት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ምዘና ስርዓትን ማዘመን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ በመታገዝ የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ አገሮች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጉባኤው ለልምድ ልውውጥ፣ ፈጠራን ለማበረታታት ብሎም የትምህርት ምዘናና የፈተና ጥራትን ለማሳደግ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ጉባኤው የኢትዮጵያን ማንሰራራት እና የብልጽግና ጉዞ ከአፍሪካና ሌሎች አህጉራት ለመጡ ተሳታፊዎች ለማሳወቅ ምቹ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጉባኤው በትምህርትና ምዘና ስርዓት ዙሪያ ያሉ እሳቤዎች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ልምዶችና ተሞክሮዎች ቀርበው ውጤታማ ውይይት እንደተካሄደባቸው ተናግረዋል።
ፍትሃዊ አሰራሮችን ማስፈን የሚያስችሉ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ትስስሮችን መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ጉባኤው ተጨማሪ ልምዶችን ለመቅስም ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል፡፡
በአውስትራሊያ ምክር ቤት የአፍሪካ የትምህርትና ምዘና አማካሪ ፕሮፌሰር ያጁራ ጃካጂ ጉባኤው ለልምድ ልውውጥ፣ ለአቅም ግንባታ እና ክህሎትን ለማካፈል ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
ናይጄሪያዊው አሞስ ዳንጉት (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ስለ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ዕውቀት ማግኘታቸውንና ኢትዮጵያ ድንቅ ሀገር መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡