በመዲናዋ ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017 (ኢዜአ):- በአዲስ አበባ በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ተተኪ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ እየተሰሩ የሚገኙ ተጨባጭ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር በመዲናዋ የእግር ኳስ ስፖርትን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በዉይይቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ከለውጡ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ዘርፍን ለማጠናከር እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።
ለዚህም በ2017 በጀት አመት በአገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ በመውጣት እውቅና ያሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ለታዳጊዎች ለሰጠው ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አስተዳደሩ ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት በሰጠው ልዩ ትኩረት 1 ሺህ 530 የሚሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውን አመልክተዋል።
እንዲሁም ታዳጊ ስፖርተኞች የሚፈሩባቸው ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ መደረጉን ጠቅሰው በተለይም በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ተተኪ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ እየተሰሩ የሚገኙ ተጨባጭ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲ በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በ2018 ዓ.ም የስፖርት ዘርፋን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ማንሳታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ስፖርታዊ ጨዋነትን ተላብሰው የታለመላቸውን አላማ እንዲያሳኩ እና በውጤታማነት እንዲያድግ ስፖርተኞች፣ የእግር ኳስ ደጋፊዎች የስፖርቱ ማህበረሰብና ወጣቶች በየአካባቢው ያለው አመራር የሚናቸውን እንዲወጡ በትጋት ለመስራት አቅደው ወደ ተግባር እንደገቡ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
ከንቲባዋ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለአገር ግንባታ የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ በመሆኑ ለስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት በትብብር መሰራቱ በስፖርቱ ዘርፍ ላይ በቀጣይም እንደ አገር እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሚናው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግለጻቸውን አመልክተዋል።
ለዚህም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በቅርርብ ፣ በቅንጅት እና በትብብር የላቀ ስራ ለማከናወን የተጀመሩትን ተግባር በማጠናከር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል ነው ያሉት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊው።