የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠናከራል -የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠናከራል -የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዳማ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ የአካል ጉዳተኞችን አካታችነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚጠናከር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ረቂቅ ፖሊሲ እና አዋጅ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምክር የተዘገጀ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንዳስታወቁት የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በተለይ የአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊ ተሳትፎ፣ አካታችነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአካል ጉዳተኞችን መብት ማክበርና ማስከበር የሰብአዊ መብት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት የሚያፋጥን መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም አካል ጉዳተኞች እኩል መብት ያላቸው በመሆኑ ያለምንም ገደብ ችሎታቸውን እና ተሰጥኦዋቸውን እንዲያሳዩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሁሉም የጋራ `ሀላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።
የዛሬው መድረክ ዋነኛ ዓላማ እነዚህን ጉዳዮች ሊመልሱ በሚችሉ የህግ ማዕቀፎች እና ፖሊሲዎች ላይ በጥልቀት ከመወያያት ባለፈ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር የተዘጋጁት ሰነዶችን በሁሉም ዘርፍ ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፣ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጸድቆ ወደ ስራ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ይህ መድረክም ፖሊሲው የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ድጋፍና አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ተስፋዬ፤ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
በተለይ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ባለስልጣኑ የጀመረውን ጥረት ያጠናክራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት በዘጋጀው መድረክ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የመንግስት ተቋማት አመራሮች፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት እና የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ናቸው።
በመድረኩ ላይ ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ በተጨማሪ፣ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ፣ አዲሱ የሕንፃ አዋጅ እና የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮል ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተመልክቷል።
በተለይም አዲሱ የሕንፃ አዋጅ የመንግስት እና የግል ሕንፃዎች፣ መንገዶች እና መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲገነቡ የሚያስገድድ መሆኑ ተገልጿል።