ኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀምን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀምን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ የመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ ገለጹ።
በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀምን ለመከላከል ተቋማዊ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ሀይል ምክትል ዋና ጸሀፊ አሸሽ ኩመር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች፣ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ፎረም እያስተናገደች ነው።
በዛሬው ዕለትም የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራች ነው።
ስብሰባው ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን በማጠናከር ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ የመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ከብሔራዊ ተቋማት ባሻገር የጋራ ቀጣናዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ሀይል ምክትል ዋና ጸሀፊ አሸሽ ኩመር በዚህ ወቅት፤ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ የአገሮችን የፋይናንስ አቅም በመሰረታዊነት የሚቀንሱ አደገኛ ወንጀሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በመጠቀም ድርጊት በየዓመቱ እስከ 90 ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣና ይህም ከአህጉሪቷ ጥቅል ሀገራዊ ምርት ሶስት ነጥብ ሰባት በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ የአገሮችን የፋይናንስ አቅም በመሰረታዊነት የሚያዳክም ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል።
የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ወንጀለኞችን ከመያዝ ባለፈ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ተጎጂዎችን መካስ፣ እምነት የሚጣልበት ተቋም መገንባት፣ ዜጎችን መጠበቅና ኢንቨስትመንትን ማሳለጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ ምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድንን አካታች፣ ፈጣንና፣ ድንበር ተሻጋሪ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም በምርምር የታገዘ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከዚህም ባለፈ የቡድኑን አቅም ማሳደግ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካ ድምፅ ጎልቶ እንዲሰማ ያስችላል ነው ያሉት።
በመሆኑም የአባል አገሮቹ ተቋማት የቡድኑን አቅም ለማጠናከር ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ሀይል የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድንን አቅም ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።