የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ተግባራዊ እርምጃ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ፕሮጀክት የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ተግባራዊ እርምጃ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ በመድረሳችን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን ሲሉ ገልጸዋል።


 

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ስምምነቱን አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ትልቅ ብስራት ነው።

የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ግብርናውን ለማሻገርና በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የተቀመጠውን አቅጣጫ ለመፈፀም የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ግብዓት መሆኑን ገልጸዋል።

ለማዳበሪያ ግዥ በየዓመቱ የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ባጠረ ጊዜ በማድረስ ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ አይተኬ ሚና እንደሚጫወትም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ስምምነቱ በመደመር እሳቤ ያሉንን የተፈጥሮ ፀጋዎች በመጠቀም ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ አለብን በሚል የተቀመጠው አቅጣጫ በተግባር እየተፈጸመ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም