ባለስልጣኑ የቡና ምርት ግብይት ሂደትን ዲጂታላይዝ ለሚያደርጉ ተግባራት ትኩረት ሰጥቷል

አዳማ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከማሳ እስከ ኤክስፖርት ድረስ ያለውን የቡና ምርት ግብይት ሂደት ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

ባለስልጣኑ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር በክልሉ የቡና ምርት ግብይት ዲጂታል ፕላትፎርም አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የግብርና ምርቶችን በዲጂታል ገበያ ለመሸጥ ከአርሶ አደሩ ማሳ ጀምሮ አመቺ የሆነ አሰራር መዘርጋት አለበት።

በተለይ የቡና ምርት ዓይነት፣ ጥራትና መጠን ከኋላ ታሪክ ጀምሮ ለማወቅ የተመዘገበ የዲጂታል ምርት ቋት ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዚህም የተረጋገጠ የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የቡና ኢንሼቲቭ ተቀርፆ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ምርትና ምርታማነቱ በሁሉም መስፈርት ማደጉን ገልጸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 469 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ መላኩንና በ2018 ዓ/ም ደግሞ ከ600 ሺህ ቶን በላይ ለዓለም ገበያ እንደሚቀርብ ገልፀዋል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ ከአርሶ አደሩ ማሳ እስከ ኤክስፖርት ድረስ በጥራት፣ በመጠንና በሚፈለገው ጊዜ ለዓለም ገበያ ለማድረስ የሚያስችል የዲጂታል አሰራርና ግብይት እየዘረጋ ነው ብለዋል።

ይህም በነባሩ የአውሮፓና አሜሪካ ገበያ ውስጥ የመወዳደር አቅምን አጠናክሮ ለማቆየትና በአዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች ተወዳዳሪ ለመሆን ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።


 

በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የግብርና ምርቶች እሴት ሰንሰለት ማኔጀር አቶ ከድር ነፎ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የሰብል፣ የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች የእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲገቡ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና በጥራት፣ በመጠንና በወቅቱ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እንዲቻል የዲጂታል ፕላትፎርም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መዘጋጀቱን ገልጿል።

በዚህም ከክልሉ ወደ ውጭ የሚላኩ የሰብል አይነቶችን ጨምሮ የቡና፣ የሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች ከምርምር ማዕከል እስከ ዘር ብዜትና አርሶ አደሩ ማሳ እንዲሁም ከመጀመሪያው ደረጃ ግብይት እስከ ኤክስፖርት ያለውን ሂደት ዲጂታል የማድረግ ስራ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

ይህም የግብርና ኤክስፖርት ምርቶች ከተቀባይ ሀገራት ፍላጎት በላይ በጥራትና በብዛት እንዲመረቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።

መድረኩ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጁ የጥራት፣ የምርትና ምርታማነት እሴት ሰንሰለትን ወጥነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚቻልበት ሂደት ላይ የጋራ ግንዛቤና አቅም ለመፍጠር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም