መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት የሰጠው ትኩረት ለስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት የሰጠው ትኩረት ለስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት የሰጠው ትኩረት ለስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ፌዴራልና የክልል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የብርጭቆ ማምረቻና የበቆሎ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት፤ በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ዲጂታል ኢኮኖሚና ኢንዱስትሪ ልማት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እምርታዊ ስኬት እየተመዘገበ ነው።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን የሚያሳድግ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንትን ምህዳር መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት የሰጠው ትኩረትም የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግርን በማስፋት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በማጠናቀቂያ የግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ የብርጭቆ ማምረቻና የበቆሎ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችም ለስራ ዕድል ፈጠራና ዕውቀት ሽግግር ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ብለዋል።
የፋብሪካዎቹ ግንባታም በአማራ ክልል የተከናወነው የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች የፈጠሩትን ዕድል የሚያመላክቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር)፤ ፋብሪካዎቹ ለክልሉ የኢንቨስትመንት አቅም በመፍጠር ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ገንቢ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።
በማጠናቀቂያ የግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ የብርጭቆ ማምረቻና የበቆሎ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎቹ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ልማትን በማስፋት የኢንዱስትሪን የምርታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስትም የ25 ዓመታት አሻጋሪ የዕድገትና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ በመቅረጽ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገትም መዋቅራዊ ሽግግርን በማሳለጥ ለክልሉ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የዴዴ ጠርሙስ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ወንድሜነህ መስፍን፤ በአራት ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚካሄደው ፋብሪካ ግንባታ ከ95 በመቶ በላይ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም ለአካባቢ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚነት መልካም አጋጣሚ ይዞ መምጣቱን አስረድተዋል።
የብራውን ፉድስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማናጀር ታደሰ ካሳሁን፤ ግንባታው 90 በመቶ ላይ የሚገኘው ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ የበቆሎ አልሚ ምግብን ጨምሮ ለቢራ ፋብሪካና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ምርቶችን የማቀነባበር ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።