ድርጅቱ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የሚፈጥሩትን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የሚፈጥሩትን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በመንግስት እየተካሄዱ ያሉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የሚፈጥሩትን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ለማ ጉዲሳ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 38ኛውን ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ጉባዔ እያካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ለማ ጉዲሳ(ዶ/ር) ፣ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ታደሰና የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ሰብሳቢው ለማ ጉዲሳ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ኢንሹራንስ ወሳኝ እና እያደገ የሚሄድ ሚና አለው።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጠናከር በመንግስት የተጀመሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚፈጥሩትን መልካም አጋጣሚዎች መጠቀም እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
ድርጅቱ ያለውን የካበተ ልምድ አሟጦ በመጠቀም፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች በመሰማራት፣ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል ።
እንዲሁም በተቋሙ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን አጠናከሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤል ታደሰ፤ ኢትዮጵያ የጀመረችው ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ የመድን ኢንዱስትሪው እድገት እንዲያስመዘግብ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በ2017 በበጀት ዓመት 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀው፤ አፈጻጸሙ አበረታች ነው ብለዋል።
ከተገኘው ገቢ 12 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከጠቅላላ መድን ዘርፍ፣ 428 ሚሊዮን ብር ከሕይወት መድን ዘርፍ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ለካሳ ክፍያ የወጣው ገንዘብ 6 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረው፤ ይህም ካለፈው ዓመት የካሳ ክፍያ ጋር ሲነፃፀር 137 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።