ቀጥታ፡

በዞኑ የማህበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል የሚያስችል ተግባር ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ):- በወላይታ ዞን በሌ አዋሳ ከተማ የማህበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል የሚያስችል ተግባር ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በዞኑ በሌ አዋሳ ከተማ አስተዳደር ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ ።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዞኑ የማህበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል የሚያስችል ተግባር ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ ነው።

በዛሬው ዕለትም  የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስገንብቶ ያስመረቀው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ አካልና የአካባቢውን ነዋሪዎች ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

ማህበሩ የህዝቡን እንግልት ለማስቀረት ስላስመረቀው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አመስግነው ህዝቡም ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ሊጠብቀው እንደሚገባም አሳስበዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ ማህበሩ መንግስት የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የሚያደርጋቸው ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተመረቀው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም ተቀናጅቶ የመስራቱ ማሳያ እንደሆነም አስረድተዋል።

ማህበሩ ከህይወት አድን ባሻገር በልማት ስራዎችም ያለውን ተሳትፎ ያጠናክራል ያሉት አቶ አበራ ዜጎች የማህበሩ አባል በመሆንና መዋጮውን በተገቢው በማዋጣት አቅሙን የማጎልበት ስራ ላይ በተገቢው እንዲሳተፉም አስገንዝበዋል።

በወላይታ ዞን የበሌ አዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አባይነህ አጫ (ዶ/ር) በበኩላቸው በከተማው የዳዳ ካሬ ቀበሌ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በንጹህ መጠጥ ውሃ እጦት ምክንያት ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ ችግሩን በመቅረፍ የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል መሆኑን ጠቁመው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት አንዲሰጥ ከነዋሪዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ታመነች ዮንኬ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጦት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲዳረጉ መቆየታቸውን አውስተው ዛሬ የተመረቀው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ችግራችንን ይቀርፍልናል።

የህዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልፀው ችግራቸውን አይተው ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እንደ አስተያየት ሰጪዋ የውሃ ፕሮጀክቱ ሳይበላሽ አገልግሎት እንዲሰጥ በጥንቃቄ እንጠቀማለን ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም