የትምህርት ምዘና ስርዓትን በማዘመን የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ አገሮች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ምዘና ስርዓትን በማዘመን የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ አገሮች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦የትምህርት ምዘና ስርዓትን በማዘመን የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ አገሮች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
"የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
42ኛውን የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ የምስራቅ አፍሪካዋ አገር ታንዛኒያ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።
ጉባኤው አባል አገሮች ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው የትምህርት ምዘና ስርዓት መገንባት የሚያስችላቸውን ልምድ ያገኙበት መሆኑ ተጠቁሟል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቷን ለማሻሻል ያከናወነቻቸው ተግባራት ለውጥ ማስገኘት ጀምረዋል።
የትምህርት ምዘና ስርዓትን ማዘመን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ በመታገዝ የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ አገሮች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጉባኤው ለልምድ ልውውጥ፣ ፈጠራን ለማበረታታት ብሎም የትምህርት ምዘናና የፈተና ጥራትን ለማሳደግ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ በጉባኤው በትምህርትና ምዘና ስርዓት ዙሪያ ያሉ እሳቤዎች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ልምዶችና ተሞክሮዎች ቀርበው ውጤታማ ውይይት እንደተካሄደባቸው ተናግረዋል።
ፍትሐዊ አሰራሮችን ማስፈን የሚያስችሉ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ትስስሮች መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል።