ቀጥታ፡

በተደረገልን ድጋፍ ከአስቸጋሪ ህይወት ወጥተን መደበኛ ኑሯችንን መኖር ጀምረናል-የገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች

ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦በመንግስትና በተለያዩ አካላት በተደረገላቸው ድጋፍ ከነበሩበት አስቸጋሪ ህይወት ወጥተው መደበኛ ኑሯቸውን መኖር እንደጀመሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በወረዳው ከአንድ ዓመት በፊት በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያስገነባቸውን 296 መኖሪያ ቤቶች ትናንት አስረክቧል።


 

በወቅቱ ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጋንታ ገዛኸኝ እና ወይዘሮ ኑሪት ብላቴ በአደጋው ከፍተኛ የሥነ ልቦናና የንብረት ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሰው፣ መንግስትና የተለያዩ አካላት ባደረጉላቸው ድጋፍ መጽናናታቸውን ተናግረዋል።


 

ከምግብና አልባሳት ድጋፍ በተጨማሪ በዘላቂነት ከችግራቸው እንዲወጡ በቀይ መስቀል የመኖሪያ ቤት እንደተገነባላቸው ገልጸው፣ ይህም የተስተካከለ መደበኛ ህይወታቸውን ለመምራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በወቅቱ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ባለቤታቸውን በሞት ያጡት ወይዘሮ ኑሪት ከአደጋው ዕለት ጀምሮ መንግስትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሲደግፏቸው እንደቆዩ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባለፈው ዓመት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ያስገነባቸውን 296 ቤቶች መርቀው ለተጎጂዎች ያስረከቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው።


 

አቶ ጥላሁን በእዚህ ወቅት እንደገለጹት አደጋው  ሁሉንም ያሳዘነ መሆኑን አስታውሰው ከችግሩ በራስ አቅምና በሌሎች እገዛ ለመውጣት የተደረገው ርብርብ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማህበር አደጋው እንደተከሰተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደርሶ ሲያደርግ ከነበረው ሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ መኖሪያ ቤቶቹን ገንብቶ ማስረከቡ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

መኖሪያ ቤቶቹ ተጎጂዎች ከስጋት ነጻ ሆነው ህይወታቸውን ተረጋግተው እንዲኖሩ ያግዛል ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ቤቶቹ በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ድርሻቸውን የተወጡ አካላትንም አመስግነዋል።

በክልሉ ለአደጋ ሥጋት የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ከቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

አደጋን በራስ አቅም ተቋቁሞ ለመወጣት የተጀመረው ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ማህበሩ አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ የዕለት ደራሽ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዱንዳ ናቸው።


 

ማህበሩ በጎፋ ዞን ኬንቾ ቡርዳ ቀበሌ ያስገነባቸውን 296 መኖሪያ ቤቶች ጨምሮ ከ352 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ጠቁመው፣ ለአደጋው ተጎጂዎቹ ማህበሩ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው የቀይ መስቀል ማህበር አደጋው ከተከሰተበት እለት ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፣ ለተደረገው እገዛም አመስግነዋል።


 

በቤቶቹ ርክክብ መርሃ ግብር ላይ የፌደራል፣ የክልሉና የዞን አመራሮች እንዲሁም የማህበሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም