የሥራ ፈጠራ ሥራችን እንዲያድግ የአቅም ግንባታ እና የፋይናንስ አቅርቦት ተደርጎልናል− ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ በመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች የአቅም ግንባታ እና የፋይናንስ አቅርቦት እንደተደረገላቸው  ገለጹ።

በዘላቂነት ሥራቸውን የበለጠ ለማስፋፋትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተጨማሪ የብድር አገልግሎት እንዲመቻችላቸውም እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ኢንተርፕራይዞችና ስታርት አፖች ጉልህ አስተዋጽኦ ስለሚያደርጉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቋል።

በፋሽን ዲዛይን ስራ የተሰማሩት ወጣት ሀናን ጀማል እና ታሪኳ ሶርሳ የስራ ሀሳብ ማመንጨት የሚያስችል ስልጠና፣ የመስሪያ ቦታና በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር የልምድ ልውውጥ የሚያገኙበት እድል ማግኘታቸውን ይናገራሉ። 


 

በቀጣይም ስራቸውን በማስፋፋት ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር ማቀዳቸውን ገልጸው፤ የአቅም ግንባታና በዘላቂነት ስራቸውን የሚያስፋፉበት የብድር አገልግሎት እንዲመቻችላቸውም ጠይቀዋል ።


 

በሥራና ክህሎት ቢሮ የተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንኩቤሽን ማዕከል አስተባባሪ ዳዊት ሀጎስ በበኩሉ፤ በማዕከሉ ስራ ፈጣሪዎች ሀሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ወደ ገበያ እስከሚገቡ ድረስ የድጋፍና የማብቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።


 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ጥቃቅን፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና ስታርት አፖች ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በመሆናቸው ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ይናገራሉ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተፈጠረው ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ የስራ እድል ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በኢንተርፕራይዞች የተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

የማደግ ሂደታቸው ከፍ ያሉትን በመለየት የመስሪያ ቦታ፣ የመሬት አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት ፣ የብድር አገልግሎት እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ እየተሰጠ ነው ብለዋል።


 

በአንዳንድ ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች እስከ ታች መዋቅሮች ባሉ አደረጃጀቶች ራሳቸው የብድር ዋስትና በመሆን የስራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በፌዴራል ደረጃ ከአጋራትና ከባንኮች ጋር የብድር አቅርቦትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ችግር ፈቺ በሆኑና ሀገር በቀል እውቀት ላይ የተመሰረቱ የፈጠራ ስራዎችን ለማልማት ትኩረት ተደርጓል።

በአዋጭነታቸው የተመረጡና ወደ ሥራ የሚገቡ 1 ሺህ 350 አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦች የሥራ ፈጠራ ባንክ ውስጥ እንደሚገኙም አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 512 ተጨባጭ የስራ ሀሳቦች የተሰባሰቡ ሲሆን፤  እነዚህን በማወዳደር ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም