ቀጥታ፡

የቀድሞ ታጣቂዎች ማህበረሰባቸውን በዘላቂ ሰላምና ልማት ለመካስ መዘጋጀት አለባቸው - አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦የቀድሞ ታጣቂዎች ማህበረሰቡን በዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ለመካስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ። 

የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን የዘላቂ ልማትና የሰላም ግንባታ አካል ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቀድሞ ታጣቂዎችን በደብረ ብርሐን ጊዜያዊ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል በተሀድሶ ስልጠና መልሶ የማቋቋም ስልጠና መሰጠት ጀምሯል።


 

በሥነ-ስርዓቱም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የፌዴራልና የክልል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተወካዮች፣  የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)÷ የክልሉ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የትኛውም ችግርና የሀሳብ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሰላም አማራጭን በመከተል በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሆኖም ጽንፈኛው ቡድን ፖለቲካዊ ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት በፈጠረው ችግር በክልሉ ህዝብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረሱን አውስተዋል።

በሌላ መልኩም የኃይል አካሄድ ህዝብን ከመጉዳት ያለፈ ጥቅም እንደሌለው የተረዱ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል በተሃድሶ ስልጠና እያለፉ መሆኑን ተናግረዋል።

በተሃድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎችም ለህዝብ አብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የሚደነቁ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችም የመንግስት የሰላም ጥሪ በመጠቀም ከስህተታቸው መመለስ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ÷ መንግስት ምንጊዜም ሀገራዊ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህብረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ የልማትና የሰላም ኃይል እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሀገራዊ የፖለቲካዊ አለመግባባቶችን እልባት ለመስጠትም ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽንና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ወሳኝ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰላም አማራጭን የሚቀበሉ አካላትንም መንግስት ግማሽ መንገድ ሄዶ በመቀበል መልሶ ለማቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ72 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና አልፈው ማህበረሰባቸውን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ብለዋል።


 

በአማራ ክልል በ2ኛው ዙር በደብረ ብርሐን፣ ኮምቦልቻና ጎንደር ጊዜያዊ ማዕከላት ከስድስት ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ስልጠና መግባታቸውን ተናግረዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ስልጠና ወደማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራም ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የደብረ ብርሐን ከተማ ከንቲባ ተወካይ ዳንኤል እሸቱ፣ ከተማዋ የበርካታ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አልሚዎች የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት ብለዋል።


 

የከተማዋ ነዋሪ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ባለቤት እንዲሆኑ እያስቻለ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ማዕከላቱ የሚገቡ የቀድሞ ታጣቂዎችም በክልሉና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሥነ-ምግባርና የሥነ-ልቦና ሥልጠና በመውሰድ ወደ የማህበረሰባቸው የሚቀላቀሉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም