የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከተረፈ ምርት በማዘጋጀት ተጠቃሚ ሆነናል -ማህበራት

ሮቤ ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከተረፈ ምርት በማዘጋጀት ለራሳቸው ከመጠቀም ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ  ማግኘት እንደቻሉ በዞኑ የጉረዳሞሌና አጋርፋ ወረዳ በዘርፉ የተደራጁ ማህበራት አስታወቁ፡፡

በዞኑ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳለጥ የሚያግዙ ዘጠኝ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀነባበርያ መዕከላት አገልግሎት መጀመራቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በጉራዳሞሌ ወረዳ  የተፈጥሮ ማዳበርያ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ሐስና ሙስጠፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ በ2017 ዓ.ም ሰርተው ለመለወጥ ፍላጎት ባላቸው 30 አባላት አማካኝነት ተቋቁሟል።

ከአባላቱ መካከል 23ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የማህበሩ አባላት ተረፈ ምርቶችን በማሰባሰብ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያውን መንግስት በአካባቢያቸው ባስገነባው ማዕከል በስፋት እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የሚያዘጋጁትን ማዳበሪያ ለምርት ማሳደጊያነት በመጠቀም ለፋብሪካ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጪ መቀነሳቸውን ገልጸዋል ።

የማህበሩ አባላት የሚያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለራሳቸው ከመጠቀም ባለፈ በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች እንዲሁም  በችግኝ ዝግጅትና በጓሮ አትክልት ልማት  ለተሰማሩ በማቅረብ ለተጨማሪ የገቢ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል ።

በአጋርፋ ወረዳ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ዜይቱ ሻፊ በበኩላቸው በአካባቢው በተቋቋመ ማእከል አማካኝነት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት የጓሮ አትክልት በማልማት ለምግብነት ከመጠቀም ባሻገር ማዳበሪያን ለሚጠቀሙ ሌሎች ግለሰቦችና ተቋማት ለሽያጭ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

አንዱን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ እስከ አንድ ሺህ ብር በመሸጥ ለገቢ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

የጉራዳሞሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሐመድ ሂሳቅ በበኩላቸው  በወረዳው ተረፈምርቶችን መልሶ በመጠቀም በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ለተሰማሩ ማህበራት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በማህበር የተደራጁ ወጣቶችና ሴቶች የሚያመርቱትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለጓሮ አትክልት ልማት ከመጠቀም ባሻገር ለሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በመሸጥ ለተጨማሪ ገቢ ማግኛነት ማዋል መጀመራቸውን አንስተዋል።

በዞኑ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳለጥ የሚያግዙ ዘጠኝ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀነባበርያ መዕከላት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ጌታቸው አበበ ናቸው።

በማዕከላቱ በማህበር የተደራጁ ከ193 በላይ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል ።


 

በጉራደሞሌ ወረዳ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶችና ወጣቶች የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን  አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም