ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል መተባበር ወሳኝ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል መተባበር ወሳኝ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ማዕቀፍ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ትብብር መፍጠር ምርጫ አይደለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች፣ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛውን የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ፎረም እያስተናገደች ነው።
ዛሬ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቦትስዋና ምክትል ፕሬዝዳንት ንዳባ ኒኮዚናቲ፣ የገንዘብ ሚኒስትር እና ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሽዴ፣ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ፋይክል ዚታ፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የሥራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ታድመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ስብሰባ በወሳኝ ሰዓት የተከናወነ ነው።
በአፍሪካ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀል ድንበር ተሻጋሪና አደገኛ አካሄድ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ አንዳንድ አገሮች በፋይናንስ ወይም በተቋማት ውስንነት ምክንያት የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድንን አለመደገፍ ችግሩን እንዲጨምር እንዳደረገው ጠቅሰዋል።
ከአፍሪካ የሚዘረፍ ሃብት የህፃናትን የመማርና የወደፊት ተስፋ የሚያጨልም፣ በሽተኞች ሕክምና እንዳያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍና ማጭበርበርን ማንም ሀገር ብቻውን መቆጣጠር እንደማይችል ተናግረዋል።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድንን መደገፍ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጠንካራ ትብብርና ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን መከላከል የሪፎርሟ አካል አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
ወንጀሎቹ ድንበር ተሻጋሪና በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸውን በማስታወስ፣ ከአፍሪካ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ትብብር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድንን ለመደገፍ ቁርጠኝነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል በማረጋገጥ በጋራ መከላከል የሚያስችል የጋራ ስትራቴጂ መቅረፅ እንደሚገባ ተናግረዋል።