ፌስቲቫሉ በቴምር ልማት ዘርፍ እንደ አገር ያለንን ዕምቅ አቅም ያሳየንበት ነው 

ሠመራ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ ፌስቲቫሉ በቴምር ልማት ዘርፍ  እንደ አገር ያለንን ዕምቅ አቅም ያሳየንበትና ለልማቱ መነቃቃት የፈጠረልን ነው ሲሉ የግብርናው ዘርፍ አመራሮች  ተናገሩ።

በሠመራ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በስኬት ተጠናቋል።

በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉት የግብርናው ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ አገራት ከመጡ እንግዶች ጋር በመሆን በአይሳኢታ ወረዳ ተገኝተው የቴምር ችግኞችን ተክለዋል፤ በአፋምቦ ወረዳ የሚገኘውን የአቢ ሐይቅንም ተመልክተዋል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፌስቲቫሉ በአገራችን መካሄዱ በዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል።

ቴምር ከፍተኛ የሥነ ምግብ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት አኳያ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከውጭ የምናስመጣቸውን የቴምር ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ረገድም ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ፌስቲቫሉ በዘርፉ የተለያዩ አገራትን ልምድ ለመቅሰም ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ አገራችን በምርቱ ላይ እሴትን በመጨመር አሁን ላይ ካለው በተሻለ ገቢ ማግኘት የምትችልበት አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል።

ጠንክረን ከሠራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሌሎች አገራት እኩል ተወዳዳሪ መሆን የምንችልበትና ትልቅ አቅም ያለን መሆኑን ያሳየንበት መድረክ ሆኖ አልፏል ብለዋል።

የአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ያሲን ዓሊ እንዳሉት ፌስቲቫሉ በቴምር ልማት ዘርፍ በአገር ደረጃ በቀጣይነት ከራስ ተርፎ ወደ ውጭ ጭምር የመላክ አቅም ያለን መሆኑን የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።


 

ተስማሚ የአየር ጸባይ፣ ለም መሬትና በቂ የውሃ ሀብት ያለን በመሆኑም ለቴምር ልማት ማደግ ያለንን አቅም ያየንበት ፌስቲቫል ነው ያሉት ሃላፊው፤ ለወደፊቱም በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በፌስቲቫሉ የቀሰምናቸው ልምዶች በቀጣይነት በዘርፉ ላይ አተኩረን የበለጠ እንድንሰራ አድርጓል ብለዋል።

በቴምር ልማት ስራ ላይ የተሠማሩት ሰኢድ ሃጂ የሱፍ በበኩላቸው አገራችን በቴምር ልማት ዘርፍ አቅም ያላት መሆኑን የውጭ ተሳታፊዎቹ በአካል መጥተውና በእርሻቸው ተገኝተው ያደነቁበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በፌስቲቫሉ እኛም የሌሎች ሀገራት ልምዶችን ቀስመን ምርታማ ለመሆን የሚያስችል ጉዞ ለመጀመር መነቃቃት ፈጥሮልናል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም