ቀጥታ፡

በግድቡ ግንባታ ላይ የታየው ትብብር  በሌሎች የልማት ስራዎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ  የታየው  ትብብርና አንድነት በሌሎችም  የልማት ስራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን  የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለስኬት መብቃቱን ተከትሎ የጋምቤላ ክልል በልማት ስራዎችና በሌሎች ኩነቶች የሚዘልቅ ሳምንታዊ መርሃ ግብር አሰናድቷል።

ዛሬ የጋምቤላ ስታዲየምን  በማጽዳት በተጀመረው መርሃ ግብሩ ሌሎች የልማት ተግባራትና የንቅናቄ መድረኮች እንደሚካሄዱበትም ታውቋል።


 

በጽዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ባደረጉት ንግግር፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማ መሆን የቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሳየው የአንድነትና የትብብር ውጤት ነው ብለዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ  የአብሮነትና የስኬቱ መገለጫ መሆኑንና የማንሰራራት ዘመን አዲስ ትርክት የተገነባበት መሆኑንም ተናግረዋል። 

ይኸን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታየውን የልማት ትብብርና የአንድነት ተሞክሮ በክልሉ አጠናክሮ በማስቀጠል የታለሙ የልማት ግቦችን ለማሳካት ተግተን እንሰራለን ብለዋል።

በተለይም የጋምቤላ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታን ለማጠናቀቅ የክልሉ ሕዝብ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ ትብብሩንና ተሳትፎውን እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ መድረሱን በማስመልከት በሚካሄደው የጽዳት ሥራ፣ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የስፖርት ማዕከላት ግንባታና ሌሎች ኩነቶችም ላይ የክልሉ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ሕብረተሰቡ በጋምቤላ ስታዲየም በመገኘት ላሳየው የጽዳት ዘመቻ ትብብር ርዕሰ መስተዳደሯ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም