ለጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ገጽታ በተገቢው ለማስተዋወቅ እና ቆይታቸውን ለማራዘም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ገጽታ በተገቢው ለማስተዋወቅ እና ቆይታቸውን ለማራዘም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለሚመጡ እንግዶች የኢትዮጵያን ገጽታ በተገቢው ለማስተዋወቅ እና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም የሚያስችሉ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ታላቅ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር በበኩሉ፤ የሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን አጀንዳ አድርጋ እያከናወነች ባለው ተግባር የቱሪዝም ዘርፉን የሚደግፍ አበረታቸ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸው፤ በመድረኩ ለመሳተፍ በርካታ እንግዶች ስለሚገኙ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ገጽታ በተገቢው ለማስተዋወቅና ቆይታቸውን ለማራዘም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም ከሆቴል ባለንብረቶች፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ከአስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ እንቁ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የሚካሔዱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ለኮንፍረንስ ቱሪዝም እድገትና ለዘርፉ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።
ለቱሪዝም ልማት የተሰጠው ትኩረት አማራጭ የመዳረሻ ስፍራዎች እንዲስፋፉ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ይህም ጎብኚዎች በፈለጉት አማራጭ የፈለጉትን ስፍራ እንዲጎበኙና ከዘርፉ የሚገኘው ጠቀሜታ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
በጉባኤው ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች ኢትዮጵያን የሚመጥን መስተንግዶና አገልግሎት እንዲያገኙ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የዝግጅት ምዕራፉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዠም ጊዜ በሚል መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ ተግባሩ የጎብኚዎችን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በአገሪቷ የሚከናወኑ የቱሪዝም ልማት ስራዎች የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር ለዘርፉ ሙያተኞች ተጨማሪ አቅምን እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ እና ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በስኬት ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ነው።