በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ስኬታማ ስራ ተሰርቷል

ባህርዳር፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ስኬታማ ስራ መከናወኑን የክልሉ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ገለጸ።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለይም በመንገድ መሰረተ ልማት የተከናወኑ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ታዛሽ ሰይፉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአዳዲስ መንገዶች ግንባታና በነባር መንገዶች ጥገና ስራ ጥሩ አፈፃፀም መታየቱን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከክልሉ መንግስትና ከፌዴራል መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በተመደበ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የነባር መንገዶች ጥገና ስራ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል ብለዋል።

‎በበጀት ዓመቱ 80 ኪሎ ሜትር አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባት አቅዶ የዕቅዱን 88 ነጥብ 9 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቅሰው፣ የድልድዮች ግንባታ እንዲሁም ከገጠር እስከ ከተማ የመንገዶች ጥገና ስራ ተከናውኗል ሲሉ ተናግረዋል። 

‎ በዚህም መሰረት 5 ሺህ 481 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገዶችን በመጠገን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰው በመንገድ ልማት ስራ በድምሩ ‎ለ15 ሺህ 228 ዜጎች የስራ ዕድል ስለመፈጠሩም ገልጸዋል።‎

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም