ግድቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መገንባት እንደምንችል ያሳየንበት የአብሮነታችን መገለጫ ነው - ነዋሪዎች

ሐረር ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መገንባት እንደምንችል ያሳየንበት የአብሮነታችን መገለጫ ነው ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል  አቶ አብዱ አብዱላዚዝ እንደተናገሩት የህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን  በጋራ የተሰለፍንበትና አንድነታችንን ያሳየንበት ነው ብለዋል።


 

ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ትርክት ማሳያ እና አብሮነታችንን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን እድገት  የሚያፋጥንና ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅምን የሚገነባ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አበራ አስናቀ ናቸው።


 

ግድቡ አንድነት ካለ መስራት እንደሚቻል የታየበት ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ሀብት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበራ ቀጣዩ ትውልድ  ሌላ ተጨማሪ ልማት እንዲያከናውን የሚያነሳሳ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ራሔል ኪዳኔ በበኩላቸው ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን ይችላሉ የሚለውን ትርክት የገነባንበት፤ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መገንባት እንደምንችል ያሳየንበት የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

የህዳሴ ግድብ መተባበርና አብሮነትን በማጽናት የማይቻል ነገር እንደሌለ የሚያሳይ ለትውልድ ተምሳሌታዊ የሆነ ስራ መሆኑን አክለዋል።


 

ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ያሳየንበትና ለልጅ ልጆቻችን በጋራ የመስራትን ተሞክሮ ያወረስንበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ አቶ ፍቃዱ ኩምሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም