ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ መሰብሰቡን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤል ታደሰ አስታወቁ።
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 38ኛውን ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ጉባዔ እያካሄደ ነው።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤል ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ ላይ ትገኛለች።
ለዚሁ ለውጥ የመድን ኢንዱስትሪው የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2017 የበጀት ዓመት ያስመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን ተናግረው፤ በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ሰብስቧል ነው ያሉት።
ከዚህ መካከል 12 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከጠቅላላ መድን ዘርፍ፣ 428 ሚሊዮን ብር ከሕይወት መድን ዘርፍ የተገኘ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ለካሳ ክፍያ የወጣው ገንዘብ 6 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረው፤ ይህም ካለፈው ዓመት የካሳ ክፍያ ጋር ሲነፃፀር በ137 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።