በቀላሉ ማግኘት እየተቻለ ችላ የሚባለው ቫይታሚን ዲ - ኢዜአ አማርኛ
በቀላሉ ማግኘት እየተቻለ ችላ የሚባለው ቫይታሚን ዲ

የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ሐኪም ዶክተር ፍጹም አሸብር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የቫይታሚን ዲ እጥረት ለተለያዩ በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል ገልጸዋል።
የቫይታሚን ዲ እጥረት የሚያስከትው ጉዳት፣ ለቫይታሚን ዲ እጥረት አጋላጭ ምክንያቶች፣ በቫይታሚን ዲ እጥረት ላለመያዝ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ባለሙያው ከታች በቀረበው መሠረት አብራርተዋል።
• የቫይታሚን ዲ እጥረት የሚያስከትው ጉዳት
O በልጆች እና ዐዋቂዎች የአጥንት ጤናማነት ላይ ጉዳት ያደርሳል።
O የጡንቻዎች ድክመት ብሎም ህመም ሊከሰት ይችላል።
O ድካም፣ የነርቭ ሥርዓት ህመም፣ የመንፈስ ጭንቀት ያጋጥማል።
O የበሽታ መከላከያ ሥርዓትን በማዳከም ለበሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል።
• አጋላጭ ምክንያቶች
O በቂ ቀጥተኛ የሆነ የፀሐይ ብርሃን አለማግኘት፤
O ከምግብ በበቂ ሁኔታ ቫይታሚን ዲ አለማግኘት፤
O ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም (ተፈጥሯዊ አጋላጭ ምክንያት ነው)፤
O አለባባስ (ሙሉ ሰውነትን ከፀሐይ በሚከልል መልኩ መልበስ)፤
O በሽታዎች (እንደ ጉበት፣ ኩላሊት ያሉ ህመሞች ከምግብም ሆነ ከፀሐይ የምናገኘውን ቫይታሚን ዲ ሰውነታችን እንዲጠቀምበት ለመለወጥ በሚደረግ ሂደት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ)።
O ውፍረት (በስብ ውስጥ የቫይታሚን ዲ መከማቸት)፤
O መድኃኒቶች (ለምሳሌ የአንቲሴዘር፣ የቲቢ፣ ስቴሮኢድስ፣ የአንጀት እንቅሰቃሴን የሚጨምሩ፣ የሃሞት ፈሳሽን ከሰውነት የሚያወጡ መድኃኒቶች)፤
• በበቫይታሚን ዲ እጥረት ላለመያዝ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ
👉 ደኅንነቱ የተጠበቀ የፀሐይ መጋለጥ (እንደ ቆዳ ዓይነት የሚወሰን ሆኖ በሣምንት ለጥቂት ጊዜያት በየቀኑ ከ10 እስከ 15 ደቂቃዎች)፤
👉 በቫይታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦች (ሳልሞን፣ ሰርዲን፣ ወተት፣ ጥራጥሬ፣ የእንቁላል አስኳሎች፣ ጉበት) መመገብ፤
👉 ከምግብ እና ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘው የቫይታሚን ዲ በቂ ካልሆነ ተጨማሪ ቪታሚን ዲ መውሰድ፤
👉 ከፍተኛ ተጋላጭነት ላለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች (አረጋውያን፣ ጽኑ ህሙማን፣ ማላብሶርፕሽን ላለባቸው ሰዎች፣ በከተሞች አካባቢ ጥቁር ቆዳ ላለባቸው ሰዎች) ምርመራ ማድረግ፤
👉 ከቤት ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ (ከቤት ውጭ በተለይም ለልጆች እና ለአረጋውያን ደኅንነቱ የተጠበቀ ጊዜን ማበረታታት)፤
👉 ክብደትን መቆጣጠር (ከመጠን ያለፈ ውፍረት ከዝቅተኛ የቫይታሚን ዲ ጋር የተያያዘ ነው)፤
👉 የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (የአጥንት እና የጡንቻን ጤና ያሻሽላል፣ ከቫይታሚን ዲ ጋር በመተባበር ይሠራል)፤
• የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለባቸው ሰዎች ምን አይነት ጥቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራል?
በአብዛኛው በከተማ የሚኖሩ ሰዎች ለቫይታሚን ዲ እጥረት ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ፍፁም፤ ለምሳሌ በመካከለኛ የትምህርት ዕድሜ ያሉ ልጆች በከተማ 61 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም በገጠር 21 ነጥብ 2 በመቶ የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባችው የጥናት ውጤት ማመላከቱን ጠቅሰዋል።
የቫይታሚን ዲ እጥረትን ለማስተካከል በግል ከሚደረጉ ጥረቶች ባለፈ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ በቃላሉ ማከም እንደሚቻልም ነው ያስገነዘቡት።
በተለይም ለዚህ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ማለትም የጉበት እና የኩላሊት እንዲሁም የማልአብዞርብሽን ችግር ያለባቸው ብሎም በክረምት ወቅት የተወለዱ ልጆች (በቂ የፀሐይ ብርሃን ስለማያገኙ ) የመድሃኒት ድጋፍ መውሰድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።