በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል

ሆሳዕና፤ ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2018 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በሆሳዕና ከተማ መክሯል፡፡
በዚህ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የሥራ ዘመን የክልሉን ፀጋ መሰረት ያደረጉ አማራጮችን በመጠቀም የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል ሥራዎች ተከናውነዋል።
ይህም ኢንተርፕራይዞችን በክህሎት ስልጠና ከመደገፍ ጀምሮ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን፣ በመስሪያና በመሸጫ ቦታ ዝግጅት፣ በብድር አቅርቦትና ተወዳዳሪ ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ለ371 ሺህ 351 ወጣቶች የሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከታቀደው በላይ ማከናወን መቻሉን አውስተዋል፡፡
በተያዘው የበጀት ዓመትም ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ነው ያመለከቱት።
የሀድያ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ሊረንሶ በበኩላቸው፤ በዞኑ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ምቹ መደላድል እየተፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት የተለያዩ የሥራ አማራጮችን በመለየት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ተግባራዊ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ከ45 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት ደግሞ የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጁ ነስሩ ናቸው።
በተያዘው በጀት ዓመትም ካለፈው የሥራ ዘመን ተሞክሮ በመውሰድ የወጣቱን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማስፋት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በሆሳዕና ከተማ በእንጨትና የብረታ ብረት ማምረቻ ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት ሄኖክ አንጁሎ፤ ዘንድሮ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ገቢ እያገኘ እራሱንና ቤተሰቡን በማስተዳደር ተጠቃሚ መሆኑን አመልክቷል።
በምክክር መድረኩ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡