በሲዳማ ክልል ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ኤች.አይ.ቪን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የመከላከል እና መቆጣጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የዘርፈ ብዙ ኤች. አይ. ቪ./ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር የ2017 በጀት አፈጻጻምና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችንና አካባቢዎችን በመለየት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም ምርመራ፣ መድሃኒት የማስጀመርና የቫይረሱን ስርጭት መጠን ለመከታተል የሚያስችል የሕክምና አገልግሎት በጤና ተቋማት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም የጤና ተቋማት የቅድመ ወሊድ ክትትል ለሚያደርጉ እናቶች የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ሰላማዊት ገልጸዋል፡፡ 

በዚህም በ2030 አዲስ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ታማሚ እንዳይኖር የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የሚያስችል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ከመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ተቆርጦ ቫይረሱ በደማቸው ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውለውን ገንዘብ በአግባቡ ሰብስቦ ከመጠቀም አንጻር ያለውን ውስንነት መፍታት የቀጣይ ትኩረት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቢሮው የኤችአይ.ቪ./ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ታረቀኝ ታሪኩ በበኩላቸው እንዳሉት ሀዋሳ፣ ይርጋለም፣ አለታ ወንዶና ወንዶገነት ከተሞች የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ከሆነባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ።


 

በከተሞቹ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ፣ የምርመራና መድሃኒት እንዲጀምሩ የማድረግ ሥራ በመስራት ኤች አይ ቪን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስድስት ወራት በተከናወነ ተግባር ከ249 በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና መድሃኒት እንደጀመሩ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች የሚሰበሰበው የ0 ነጥብ 5 ከመቶ የኤድስ ፈንድ በተገቢው ከመሰብሰብና ከመጠቀም አንጻር በሚታዩ ክፍተቶች ላይ መድረኩ ትኩረት ሰጥቶ መምከሩንም ጠቅሰዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ለኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ተጋላጭ ከሆኑት ቀዳሚ መሆኗን የጠቀሱት የሃዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ይርዳቸው አናቶ ፣ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የታገዘ የምርመራና የግንዛቤ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡


 

ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለይቶ የሚከናወኑ የምርመራና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እስከ ጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት እንደሚዘልቅ ጠቅሰው፣ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሰሩ ነው ብለዋል። 

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ ከክልል ጀምሮ ባሉ መዋቅሮች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀትና ሽልማት የመስጠት መርሃ ግብርም ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም