የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሽግግር ኢኒቬቲቭ የዘርፉ ተዋንያንን የፕሮጀክት አፈፃፀም ለማሳደግ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሽግግር ኢኒቬቲቭ  የዘርፉ ተዋንያንን የፕሮጀክት አፈፃፀም በማሳደግ በሌሎች አገራት ለመሳተፍ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል ስምንተኛውን የመንገድ ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ አካሒዷል፡፡


 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡

ብቃት ያለው ውጤታማና ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር አገር አቀፍ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሽግግር ኢኒቬቲቭ ገቢራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ ወጭና ጥራት ማጠናቀቅ የሚያስችል የፕሮጀክት አፈፃፀም እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የተቀመጡ ስትራቴጂዎች የዘርፉን ተወዳዳሪነት እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና ባለሙያዎች በአፍሪካ አገሮች ጭምር በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብድራህማን በበኩላቸው፤ የመንገድ ዘርፍ በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከለ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ በጀት የሚመደብላቸው ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት የሚመልሱ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሪፎርሙ የመንገድ ምርምርን በማጠናከር የፕሮጀክት አፈፃፀም አቅምን ያሳድጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወርቁ አስራቴ (ዶ/ር)፤ የመንገድ ምርምር ዘርፉን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የፕሮጀክት አስተዳደር፣ የሀብት አጠቃቀም ውስንነቶች እንደነበሩ በማስታወስ፤ ዘርፉን በምርምር መደገፍ አስፈልጓል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም