ኢትዮጵያ በቴምር ልማት እምቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ማረጋገጥ ችለናል - የቴምር ፌስቲቫል ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቴምር ልማት እምቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ማረጋገጥ ችለናል - የቴምር ፌስቲቫል ተሳታፊዎች

ሰመራ ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቴምር ልማት እምቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን በማየት ማረጋገጥ ችለናል ሲሉ በዓለም አቀፉ የቴምር ፌስቲቫል ላይ የተሳተፉ የተለያዩ አገራት ተወካዮች ተናገሩ።
የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ለሶስት ቀናት ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል።
በፌስቲቫሉ ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ የግብርና ሃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በክልሉ የዘርፉን ልማት ጎብኝተዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ አገራት ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ለቴምር ልማት ምቹ የአየር ንብረት፣ ሰፊ መሬትና ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ አሰራር ያላት መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቴምር ልማት እምቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን በአካል ተገኝተን በማየት ማረጋገጥ ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል ከሜክሲኮ የመጡት ሆርኬ አናያ፤ ከፌስቲቫሉ በተጓዳኝ በአፋር ክልል በነበረን ጉብኝት ኢትዮጵያ በተለይም በቴምር ልማት ምን ያክል እምቅ አቅም እንዳላት የተረዳንበት ነው ብለዋል።
በአካባቢው በቴምር ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሰራ ከራስ አልፎ ለሌሎችም የሚጠቅም ምርት የሚገኝበት መሆኑን ጠቁመው፤ የተጀመረው እንቅስቃሴም ይህንኑ ለማሳካት የሚያስችል ጅምር መሆኑን አንስተዋል።
ከሞሮኮ የመጡት አብዱላህ ሙስጠፋ፤ የፌስቲቫሉ መካሄድ ከተለያዩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት እድል የፈጠረና የኢትዮጵያንም እምቅ አቅም ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሥነ ምግብነት ጠቀሜታ ያለው ቴምር ሰፊ የገበያ አማራጭ እንዳለው ያነሱት አብዱላህ፤ በትብብርና ትኩረት ሰጥተን በማልማት ከኢትዮጵያም ባለፈ ለሌሎች አገራት የሚተርፍ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከተርኪዬ በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉት አማን ከድርበሺር፤ በዘርፉ የሚዘጋጁት መሰል ፌስቲቫሎችና ዐውደ ርዕዮች ቴምርን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን እንድናለማ ያግዘናል ብለዋል።