የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በዓለም አቀፍ የገበያ ሥርዐት ውስጥ ተወዳዳሪነቱን ጠብቆ ለመቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው 

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በዓለም አቀፍ የገበያ ሥርዐት ውስጥ ተወዳዳሪነቱን ጠብቆ ለመቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ ገለጹ።

የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በላቦራቶሪ አስተዳደር ሥርአት "ISO-17025" ዛሬ የዕውቅና የምስክር ወረቀት አግኝቷል።

በሀዋሳ ከተማ ዛሬ በተካሄደ የእውቅና አሰጣጥ ሥነሥርዐት ላይ የኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ የምሥክር ወረቀቱን ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ተቀብለዋል።


 

በዚህ ወቅት ሥራ እስኪያጁ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ዓለም አቀፍ የገበያ ሥርዐት ውስጥ ተወዳዳሪነቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑን ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተፈላጊነት የሚያሳድጉ የISO የእውቅና ምስክር ወረቀቶችን በተለያዩ ዘርፎች ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም ዞኑ የፍሳሽ ውሃ አወጋገድ ሥርአቱ በአካባቢው አየር እና ማህበረሰብ ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን የሚያረጋግጥ የISO-14001 የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በውስጡ በሥራ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ምርቶቻቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተቀባይነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ ለኢንቨስትመንት ወደ ዞኑ የሚመጡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም ፍላጎታቸው ጨምሯል ብለዋል፡፡

ዛሬ በላቦራቶሪ አስተዳደር ሥርዐት የተገኘው የISO-17025 ደግሞ ለዞኑ ተጨማሪ ጥቅምና ዕውቅና እንደሚያስገኝ የተናገሩት አቶ ማቴዎስ፣ ከዚህ በፊት የሚጠቀሙበትን ውሃ ለማስፈተሽ ናሙና ወደ ውጭ ሀገር የሚልኩ ኩባንያዎች እዚሁ አስፈትሸው ለመጠቀም እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል፡፡

ከዞኑ ውጭ ላሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ኢንዱስትሪዎች የፍተሻ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዞኑ እና በዞኑ ያሉ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ዕውቅናቸውና ተወዳዳሪነታቸው ይበልጥ እንዲጨምር ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይ በአጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት የሚያደርገውን የISO-9001 ዕውቅና ምስክር ወረቀት ለማግኘት ዞኑ የዝግጅት ሥራውን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡፡

በኃይል አጠቃቀም ሥርአት ላይ እንዲሁ ተጨማሪ ዕውቅና ለማግኘት በዞኑ በኩል የዝግጅት ሥራዎች መጀመራቸውን ነው አቶ ማቴዎስ ያስታወቁት፡፡

በኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት የላቦራቶሪ አክሪዲቴሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌቴ ብርሀን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በላቦራቶሪ አስተዳደር ሥርአቱ  ባሉ ሶስት መለኪያዎች መሰረት የዕውቅና ምስክር ወረቀቱን እንዳገኘ አስረድተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዓለም ዓቀፍ የላቦራቶሪ አክሪዲቴሽን ትብብር አባል መሆኑን አስታውሰው፣ ዞኑ ያገኘው የምስክር ወረቀት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት አርአያ የሚሆን ሥራ እየሰራ መሆኑንም አቶ ጌቴ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም