በዩኒቨርሲቲው የተሰጠን ስልጠና የእውቀት አድማሳችንን አስፍቶልናል - ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲው የተሰጠን ስልጠና የእውቀት አድማሳችንን አስፍቶልናል - ተማሪዎች

ወልዲያ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡- በክረምቱ ወራት በዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና የእውቀት አድማሳቸውን ማስፋት እንዲችሉ እንዳገዛቸው ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተናገሩ።
ወልዲያ ዩንቨርሲቲ በቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከሉ ባለፉት 2 ወራት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህድስናና ሒሳብ ትምህርቶች ያሰለጠናቸውን ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ዛሬ ሸኝቷል።
ተማሪዎቹ በየትምህርት ደረጃቸው የላቀ ውጤት በማምጣት ተመልምለው በዩኒቨርሲቲው የሰለጠኑ እንደሆነ ተመልክቷል።
ስልጠናውን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቀችው ረድኤት መኮንን በሰጠችው አስተያየት፤ ቀደም ሲል በትምህርት ቤቷ በንድፈ ሀሳብ ያገኘችውን እውቀት በዩኒቨርሲቲው የክረምት ስልጠና ማዳበር እንደቻለች ተናግራለች።
በዩኒቨርሲቲው የላቦራቶር፣ የማጣቀሻ መጻህፍት፣ የኮምፒውተር አገልግሎት የተሟሉለት በመሆኑ የዕውቀት አድማሴን አስፍቶልኛል ስትል ገልጻለች።
ሌላው ሰልጣኝ ኤፍሬም መካሻ በበኩሉ፤ በዩኒቨርሲቲው የተሰጠው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርት የቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲሰራና የእውቀት አድማሱን ማስፋት እንዲችል ያገዘው መሆኑን ተናግሯል።
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ማርዬ በለጠ (ዶ/ር) በሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በስልጠናው ተማሪዎች በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
ስልጠናውን የወሰዱት ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም እንደ ክፍል ደረጃቸው በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና በሒሳብ ላይ ያተኮረ ትምህርት በብቁ መምህራን መስጠት መቻሉን አስረድተዋል።
ዩኒቨርስቲው ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ 150 ተማሪዎች ለስልጠናው የኮምፒውተርና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ከማሟላት በሻገር የምግብ፣ የመኝታ፣ የህክምናና የመጓጓዣ ሙሉ ወጪዎችን መሸፈኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ለሰልጣኝ ተማሪዎች በያሉበት አካባቢ ዩኒቨርሲቲው ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ማርዬ በለጠ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።