የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ሳይንስና ቴክኖሎጂን በተሻለ መንገድ ለመረዳት አስችሎናል - ታዳጊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ሳይንስና ቴክኖሎጂን በተሻለ መንገድ ለመረዳት አስችሎናል - ታዳጊዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ሳይንስና ቴክኖሎጂን በተሻለ መንገድ ለመረዳት የሚያስችል ግንዛቤን ያስጨበጣቸው መሆኑን ታዳጊዎች ገለፁ።
አምስት የዐውደ ርዕይ ምድቦችን የያዘው የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ መከፈቱ ይታወሳል።
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ምላሽ፣ ግብርና ቴክኖሎጂ፣ የውኃ ኃይል እና ኢነርጂ፣ ኤሮኖቲክስ እና አቪየሽን ላይ ያተኮሩ የዐውደ ርዕይ ምድቦች ይዟል።
ኤግዚቢሽኑን ሲጎበኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳጊዎች ጉብኝቱ የሰው ሰራሽ አስተውህሎትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በተሻለ መንገድ ለመገንዘብ እንደሚረዳ አብራርተዋል።
ቋሚ ኢግዚቢሽኑን ሲጎበኝ ያገኘነው ህፃን ሞገስ ሚልኪያስ በኤግዚቢሽኑ ሮቦትና ሌሎች የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የተለያዩ ዘርፎች ቴክኖሎጂዎችን መመልከቱን ተናግሯል።
በእረፍት ጊዜው ኤግዚቢሽኑን መጎብኘቱ በትምህርት ቤት የተማራቸውን ነገሮች በተሻለ መንገድ እንዲረዳ እንዳስቻለው ገልጿል።
ከአሜሪካ እንደመጣ የተናገረው ባርክኤል ዳዊት በበኩሉ በቋሚ ኤግዚቢሽኑ የተመለከታቸው ቴክኖሎጂዎች እንዳስደነቁት ነግሮናል።
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለን እውቀት ለማጎልበት የሚረዳ ነውም ብሏል።
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያ በላቀ እድገት ላይ መሆኗን እንድገነዘብ አድርጎኛል ያለችው ደግሞ ሌላዋ ከአሜሪካ የመጣችው ኬብሮን ዳዊት ናት።
ከሃዋሳ የመጣው ሶፎንያስ ተስፋዬ በበኩሉ ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ስለ ሰው ሰራሽ አስተውህሎትና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ውሃና ኢነርጂ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደረዳው ይናገራል።
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ትውልዱን ለፈጠራ የሚያነሳሳና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን ለመወሰን የሚረዳ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዳዊት ዓለሙ ናቸው።
አስተያየት ሰጪዎቹ ተማሪዎች በተለይ በቀሪ የእረፍት ጊዜያቸው ኤግዚቢሽኑን በመጎብኘት የተሻለ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት እንዲጨብጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአንድነት ፖርኮች ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ጌታቸው በየነ በበኩላቸው፤ የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን አሁን ላይ ያለውንና የወደፊቱን የቴክኖሎጂ ሁኔታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሳይንስ ለአገር ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ኤግዚቢሽኑ ትውልዱ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ተገንዝቦ የፈጠራ ክህሎቱን እንዲያዳብር የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።