የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የተጀመሩ አገራዊ ውጥኖች ከዳር እንዲደርሱ መረባረብ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የተጀመሩ አገራዊ ውጥኖች ከዳር እንዲደርሱ ልንረባረብ ይገባል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት ዘሃራ ዑመድ ገለጹ፡፡  

የፓርቲው ሴቶች ክንፍ ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና 2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ  ውይይት አካሄዷል፡፡ 

ክንፉ ሴቶችን በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ ባከናወናቸው ተግባራት፣ በተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል፡፡


 

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዘሃራ ዑመድ በውይይቱ ማጠቃለያ የበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት ከዳር ለማድረስ የምንረባረብበት ነው ብለዋል፡፡ 

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዐሻራችንን ያሳረፍንበት ትልቁ ውጤታችን ነው  ብለዋል።

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ዓለም ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ኢኒሼቲቩ በተሟላ መልኩ እንዲተገበር ሚናችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡  

የብሔራዊ መታወቂያ ጉዳይን አጀንዳ ማድረግ እና ግንዛቤ ማስፋት ላይ ይበልጥ መስራት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡


 

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንትና የክንፉ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ በበኩላቸው፤ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ ሴቶች የጎላ ሚና እንዲጫወቱ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ 

በሰላም ጉዳይ ውጤት እያመጣ ያለውን የሴቶች ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰራ በመጥቀስ ሴቶች በልማትና በፖለቲካ ተሳትፎ የተሻለ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡  

የክንፉ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን፤ ክንፉ በየመስኩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያከናወናቸው ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡   

የውጤቱን አፈጻጸም ወጥ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም በቅንጅት የመስራት ጉዳይ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም