ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትጋት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትጋት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በ2018 ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ 


 

በመዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሙስናን በመከላከል አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ከምዝበራ ማዳን መቻሉ በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በመዲናዋ ሙስናን ለመታገል ከሚወሰዱ እርምጃዎች በተጓዳኝ ሌብነትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመገንባት እየተሰራ ነው። 

በከተማዋ የሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የስነ-ምግባር ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ 

ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ በመንደፍ በሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስናን በመከላከል ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል። 

በዚህም በአስቸኳይና በመደበኛ የሙስና መከላከል ሥራ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት ከምዝበራ ማዳኑን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ብልሹ አሰራር የፈጸሙ ሠራተኞች፣ አመራር አባላት እና ባለጉዳዮች በህግ እንዲጠየቁ ማድረጉንም ጠቁመዋል። 

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መቅደስ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በሥነ-ምግባር ግንባታና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።  


 

በዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ የእምነት ተቋማት እና በመንግሥትና በግል ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።  

ኮሚሽኑ የሀገርና የሕዝብን ሀብትና ንብረት ከምዝበራ ለማዳን በሚያከናውነው ተግባር ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በክፍለ ከተማ ደረጃ በሥነ-ምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ዘርፎች አመርቂ የሚባሉ ስራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሥነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና መከታተያ ክፍል ቡድን መሪ ወይዘሮ ስንታየሁ ወዳጆ ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሥነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና የስራ ሂደት መሪ ስለሺ አሰፋ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ለሚገኙ ፈጻሚዎች በጸረ ሙስና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡


  

የየካ ክፍለ ከተማ የሥነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ቡድን መሪ ወይዘሮ ናናቲ ገስሙ በበኩላቸው፤ ሙስናን ከመከላከል አኳያ የሁሉም ተሳትፎና እገዛ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡


 

ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስነ-ምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት እውቅና ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም