ኢትዮጵያ ዘመኑን የሚዋጅ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓትን ተግባራዊ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘመኑን የሚዋጅ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓትን ተግባራዊ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የሚጣጣም እና ዘመኑን የሚዋጅ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን ተግባራዊ እንደምታደርግ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን የሚከለክለው አዋጅ ከስድስት ወር በኋላ ይተገበራል ብለዋል።
የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።
ባለስልጣኑ አዋጁ ተግባራዊ በሚሆንበት አግባብ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት እየተሰጠ ባለው የስልጠና መድረክ ላይ ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት አዋጁ ከያዛቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የፕላስቲክ ቆሻሻ አያያዝና የአወጋገድ ስርዓት ይገኝበታል።
የፕላስቲክ ውጤቶች በመሬት ውስጥ ሳይበሰበሱ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ በመሆናቸው ለአካባቢ ብክለት መንስዔ፣ ለሰው ልጅ ጤና ደግሞ ጉዳት እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የሚጣጣም እና ዘመኑን የሚዋጅ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ማዘጋጀቷን ገልጸዋል።
በአዋጁ መሠረትም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ ማምረትና ለገበያ ማቅረብ እንደማይቻል አመልክተዋል።
ይህም ከስድስት ወራት በኋላ በመላው ሀገሪቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በአካባቢም ሆነ በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የማያደርሱ ምርቶችን ለማቅረብ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከአምራች ዘርፉ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የዛሬው ስልጠናም አዋጁ በአግባቡ እንዲፈጸም ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ እንዲይዙ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ ጽዱ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም አስታውቀዋል።