ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአምራች ኢንዱስትሪ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአምራች ኢንዱስትሪ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአምራች ኢንዱስትሪ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት አስተማማኝነት እና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ያስችላል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የመተባበር፣ የአንድነትና በጋራ የመቆም ጥረት ውጤት ነው።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች መሆኗን አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት አልምቶ ከመጠቀም አኳያ ውስንነቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአመራር ቁርጠኝነትና የህዝብ አይበገሬነት የታየበት መሆኑን አመልክተው፤ ዓባይን አልምቶ የመጠቀም የዘመናት ቁጭትን የሚመልስ እና የጋራ ትርክትን የመገንባት ውጥን የሚያሳካ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።
ኢትዮጵያንና ዓባይን ለማራራቅ ሲሰራ የቆየን ታሪክ በመቀልበስ የዚህ ትውልድ አኩሪ ታሪክና ድል መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት የአገሪቷን እድገት የሚያፋጥኑ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ሃብትን ወደ ጥቅም መቀየር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የኢንዱስትሪ ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ትኩረት እንደተሰጣቸውም አክለዋል።
በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ማንሰራራት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ ለአምራች ኢንዱስትሪው እድገት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ይህ ስኬት በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውስንነትን በማቃለል አምራች ኢንዱስትሪው ምርትና ምርታማነቱ እንዲጨምር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ አምራች ኢንዱስትሪውን ማዕከል ያደረገ እድገት ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።
እንዲሁም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የታየው የአመራር ቁርጠኝነትና የህዝብ አይበገሬነት ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍትሃዊ ጥያቄዋን አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ስኬት፤ የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ፤ የደም ጠብታ፣ የላብ ጠብታ፣ የዕንባ ጠብታ፣ የውኃ ጠብታ ድምር ውጤት መሆኑን፣ ይህ ግድብ ህያው ምልክት ሆኖ ለትውልድ ሲመሰክር ይኖራል በማለት በቅርቡ ገልጸውታል።