የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አፍሪካውያን ሀብታቸውን በራሳቸው ማልማትና መጠቀም እንደሚችሉ የሚያበስር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አፍሪካውያን ሀብታቸውን በራሳቸው ማልማትና መጠቀም እንደሚችሉ የሚያበስር ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አፍሪካውያን ሀብታቸውን በራሳቸው ማልማትና መጠቀም እንደሚችሉ የሚያበስር ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡
አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያበስር ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የቅኝ ግዛት እሳቤዎች ቦታ የላቸውም ያሉት አምባሳደር ነብያት፣ ኢትዮጵያ ለናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ገቢራዊነት ጠንክራ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ሀብታቸውን ማልማትና መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከቀጣናው አገሮች ባሻገር ሌሎች አፍሪካውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ አህጉራዊ ሜጋ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጋራ ሀብቶችን በጋራ መጠቀም ይገባል የሚል ጽኑ አቋም እንዳላት የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ እና ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በስኬት ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን ጨምረው ገልጸዋል።
በጉባኤው ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም አፍሪካዊ የሆነ የጋራ መፍትሄ የሚቀይሱበት መድረክ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
አፍሪካ በብራዚል በሚካሄደው 30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የራሷን ድምጽ ይዛ ለመቅረብ ወሳኝ አጀንዳዎችን የምትለይበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አጋርነትና ትብብርን ለማስፋትና ለማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደሩ፤ኢትዮጵያ አጀንዳ በመቅረጽና መሪ ተዋናይ ሆና የምትቀርብበት ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከልና ለመቋቋም የወሰደቻቸው እርምጃዎችና የተገኙ ውጤቶች ለዓለም እንደምታቀርብ ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ ጉባኤ "ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትህን ለመሻት አህጉር ተሻጋሪ አጋርነት" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካና ካሪቢያን አገሮች በደቡብ ደቡብ የትብብር መንፈስ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት እና ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትብብር ለማሳደግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
በዓለም የፋይናነሰ ስርዓት አስተዳደር፣ በቱሪዝም፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት አፍሪካና ካሪቢያን በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የካሪቢያን ባለሀብቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በተፈጠሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ መድረኩን ትጠቀምበታለች ብለዋል፡፡