የህግ አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ የማድረግ ስራ ትኩረት አግኝቷል - የክልሎች የፍትህ ዘርፍ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህግ አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ የማድረግ ስራ ትኩረት አግኝቷል - የክልሎች የፍትህ ዘርፍ ኃላፊዎች

አዳማ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ የህግ አገልግሎትን እስከ ወረዳ ድረስ በማውረድ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ የማድረግ ስራ ትኩረት ማግኘቱን የክልሎች የፍትህ ዘርፍ ኃላፊዎች ገለጹ።
የፍትህ ተደራሸነትን ለማስፋትና የዳኝነት አገልግሎትን ለማሳደግ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ዙሪያ ኢዜአ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የፍትህ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አደርጓል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቆጭቶ ገብረማርያም፤ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለይቶ በማውጣት የመፍትሄ ሀሳብ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የህግ አገልግሎትን ወደ ታች ድረስ በማውረድ የወረዳ ፍርድ ቤቶች እንዲጠናከሩ የሚያደርግ የአሠራር ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ትልቅ እምርታ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ተገልጋዮች ፍትህ ፍለጋ ወደ ዞን ማእከላት የሚያደርጉትን ምልልስ በማስቀረት በአቅራቢያቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል መፍጠሩን አመላክተዋል።
ይህንን ተከትሎ የሕዝብ አመኔታ ያተረፈ የዳኝነት ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መቻሉን አውስተዋል።
እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሁኑ ወቅት በምድብ ችሎትና በተዘዋዋሪ ችሎት ማዕከሎች በወንጀልና በፍትሐብሄር ጉዳዮች የዳኝነት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በየደረጃው በተሰጣቸው ስልጣን ወሰን መሠረት ክልሉ ውስጥ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አቶ ቆጭቶ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ዋሴ፣ በሕግና ፍትህ ዙሪያ በሚካሄዱ ጥናትና ምርምር ስራዎች የፍትሕ ስርዓቱ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
በዳኝነት፣ በአቃቢ ህግና በሌሎችም የህግ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ስራዎች በሥራ ሂደታቸው ላይ ሊያጋጥም የሚችለውን የህግ አተረጓጎምና አተገባበር ችግር በመፍታት ለህብረተሰቡ ፍትሀዊና ተአማኒ አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን አስረድተዋል።
በክልሉ የሚገኙ የፍትህ አካላት ባለሙያዎችን የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም ለመገንባት የሥራ ላይ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠቱን ገልጸዋል።
ይህም በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት እንዲሁም በሥነ-ምግባሩ ብቁ የሆነና የተሟላ ስብዕና ያለው የዳኝነት እና የፍትህ አካላት አመራር እና ባለሙያ ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን አቶ አብዲሳ አብራርተዋል።
የፌዴራል የሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ባከናወናቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ በኢንስቲትዩቱ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ እና በ2018 ዕቅድ ላይ ለመምከር ያዘጋጀው አውደ ጥናት ለሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።