ኮሌጁ የዕውቀት ሽግግር እና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ ዘመናዊ ፖሊሳዊ አገልግሎት ተግባራዊ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ የዕውቀት ሽግግር እና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ ዘመናዊ ፖሊሳዊ አገልግሎት ተግባራዊ እያደረገ ነው

አዳማ ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የዕውቀት ሽግግር እና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ ዘመናዊ ፖሊሳዊ አገልግሎትን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገለፀ።
ኮሌጁ በወንጀል መከላከል፣ በፖሊሳዊ አሰራርና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ባከናወናቸው የጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በአዳማ እያካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ ላይም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አበበ ለገሰ እንደገለፁት፤ ኮሌጁ የዕውቀት ሽግግርና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ ዘመናዊ ፖሊሳዊ አገልግሎትን ተግባራዊ እያደረገ ነው።
በተለይ የሰለጠነ የፀጥታ ኃይልን በማብቃት የሰው ሀብት ልማት ስራን ከማከናወን ጎን ለጎን የወንጀል መከላከልና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮሌጁ ያከናወናቸው የጥናትና ምርምር ውጤቶች የስልጠና ስርዓቱን አካሄድ ለማሻሻል፣ የፍትህ አገልግሎትና የወንጀል መከላከል ስራን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ጎሳዬ ከበደ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮሌጁ 22 የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ጥናቶቹ በፖሊስ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ከመሙላት ባለፈ የሰላምና ልማት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ አሰራር ከምንጩ ለማስወገድ የተካሄዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ጥናቶቹ የወንጀል አይነቶችን በመለየት የህዝቡን የሰላም ባለቤትነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችሉ መሆናቸውንም አክለዋል።
የኮሌጁ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ኮማንደር ፍቃዱ ታፈሰ እንደገለፁት፤ በኮሌጁ የማማከር፤ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የወንጀል መከላከል የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።
የጥናትና ምርምር ስራዎቹ በተለይ በክልሉ የፀጥታ ሁኔታና ወንጀል መከላከል፣ የፀጥታ ሃይሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም ማጎልበት ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል።
በዚህም ወንጀልን ቀድሞ መከላከልና ከተከሰተም ፈጥኖ ፍትህ እንዲገኝና የህብረተሰቡን የደህንነት ስጋት ለማስወገድ የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኮሌጁ በክልሉ እየተከናወነ ያለውን ፖሊሳዊ አደረጃጀት፣ አሰራርና አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ ግብዓቶችን በጥናትና ምርምር በመለየት ዘርፉን የማዘመን ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም በክልሉ የተመረጡ አምስት ከተሞችና ሁለት ዞኖችን የፖሊሳዊ አገልግሎት ሞዴል ለማድረግ የተለያዩ ተሞክሮዎች የተካተቱባቸው ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የአውደ ጥናቱ ዓላማም የጥናትና ምርምር ስራዎቹን በግብዓት በማዳበር ለአስፈፃሚውና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መሆኑንም ገልፀዋል።