የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያስገነባቸውን 296 ቤቶች አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያስገነባቸውን 296 ቤቶች አስረከበ

ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 22/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባለፈው ዓመት ድንገት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያስገነባቸውን 296 ቤቶች አስረከበ።
ማሕበሩ በወረዳው ኬንቾ ቡርዳ ቀበሌ ያስገነባቸውን ቤቶች ለተጎጂ ወገኖች ያስረከበው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት ነው።
በርክክቡ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር ፤ የክልሉ መንግስትም ጉዳቱ በደረሰበት አካባቢ ላሉ 150 አባወራዎች መኖሪያ ቤት ሰርቶ ቀደም ብሎ ማስረከቡን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ጉዳቱ ለደረሰባቸው ወገኖች በወቅቱ ደርሶ ሰብአዊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ በማውሳት ምስጋና አቅርበዋል።
ቤት መስራት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ተጎጂዎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ በበኩላቸው፤ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርጉትን ሰብአዊ ድጋፍ ለማጠናከር ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በጎፋ ዞን አደጋው በደረሰበት ወቅት ቀድመው በመድረስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይም ወገኖችን በቅርበት ለመርዳት እንተጋለን ብለዋል።