በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተገነቡ የውሃ ተቋማት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ሽፋንን አሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተገነቡ የውሃ ተቋማት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ሽፋንን አሳድገዋል

ጎንደር፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተገነቡ 164 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት የተደራሽነት ሽፋንን ማሳደግ እንዳስቻሉ የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ማሩ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውሃ ተቋማቱ በመንግስት በሕብረተሰቡና በአጋር አካላት የበጀትና የቁሳቁስ ድጋፍ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ናቸው፡፡
ለአገልግሎት ከበቁት የውሃ ተቋማት መካከል 146 የእጅ ጉድጓዶች ዘጠኝ መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓዶችና ሶስት በዘመናዊ መንገድ የጎለበቱ ምንጮች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የውሃ ተቋማቱ ከ81 ሺሕ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ የዞኑን የንፁሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ሽፋን ከነበረበት 58 በመቶ ወደ 62 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡም ለተቋማቱ ግንባታ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አውስተዋል፡፡
በተጨማሪም በብልሽት ቆመው የነበሩ አንድ ሺሕ 676 የውሃ ተቋማት ከከባድ እስከ ቀላል የጥገና ስራ በማከናወን ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
በውሃ ተቋማቱ ግንባታ ሂደትም ለተደራጁ ወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
በወገራ ወረዳ የኮሶዬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አምበርብር ሞላ፤ ከዚሕ ቀደም በነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ንጽሕናው ያልተጠበቀ ወራጅ ውሃ በመጠቀም ለውሃ ወለድ በሽታ ሲጋለጡ እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡
መንግስት ደጃፋችን ላይ ባስገነባልን የእጅ ጉድጓድ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናችን ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት አቶ አምበርብር፤ የውሃ ተቋሙን በባለቤትነት ጠብቀው ለመንከባከብ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ በለሳ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ማሪቱ በላይነሕ በበኩላቸው፤ ሴቶችና ሕጻናት ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ በመጓዝ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር አውስተዋል።
አሁን ላይ በአቅራቢያቸው የተገነባው የውሃ ተቋም የነበረባቸውን እንግልት ከመቀነስ ባሻገር የንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ መምሪያው እንዳስታወቀው፤ በአዲሱ የበጀት ዓመት የማዕከላዊ ጎንደር ዞንን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የድርጊት መርሃ ግብር እየተዘጋጀ ነው።