የቀድሞ ታጣቂዎች ማህበረሰቡን በልማት ለመካስ መዘጋጀት አለባቸው - አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ የቀድሞ ታጣቂዎች ማህበረሰቡን በዘላቂ የሰላም ግንባታ እና በልማት ለመካስ ሊዘጋጁ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቀድሞ ታጣቂዎችን በደብረ ብርሐን ጊዜያዊ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል በተሀድሶ ስልጠና መልሶ የማቋቋም ስልጠና መሰጠት ጀምሯል።

በተሀድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የፌደራልና የክልል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)፥ የክልሉ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የትኛውም ችግርና የሀሳብ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሰላም አማራጭን በመከተል በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሆኖም ጽንፈኛው ቡድን ፖለቲካዊ ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት በፈጠረው ችግር በህዝብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረሱን አውስተዋል።

በሌላ በኩል የኃይል አካሄድ ህዝብን ከመጉዳት ያለፈ ዓላማ እንደሌለው የተረዱና ለሰላም ቅድሚያ የሰጡ በርካታ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ተሃድሶ ስልጠና እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎቹ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ እየተቀላቀሉ ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን፥ ለህዝብ አብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በጫካ የሚገኘው ጽንፈኛ ኃይል ከዚህ ቀደም የአማራን ህዝብ የሽምግልና እሴት በሚንድ መልኩ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ህፃናት ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙን ገልጸዋል።

እንዲህ ያለው የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ከሞራል ፍጹም ያፈነገጠና የሚያደርሰው ማህበራዊና ሰብዓዊ ጉዳትም ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ሊቃወመውና እንዳይደገም ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ህዝብን ከድህነት ወደ ተሟላ ብልፅግና የሚያሸጋግር የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ በመቅረጽ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ለስኬቱም ህዝቡ፣ የቀድሞ ታጣቂዎችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም