ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የመንግስት ሰራተኞች የደምወዝ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር ይደረጋል

ጋምቤላ፤ ነሐሴ 22/2017 (ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል ከመጪዎቹ በዓላትና ለመንግስት ሰራተኞች እንዲደረግ የተገለጸውን የደምወዝ ማሻሸያ ጋር ተያይዞ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ኛሞች ጊል ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከመጪዎቹ ህዝባዊ በዓላትና ለመንግስት ሰራተኛው ከሚደረገው የደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቢሮው ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ ነው።

በተለይም መንግስት ከመስከረም ወር 2018 ጀምሮ የሰራተኛውን ኑሮ ለማሻሻል የሚያደርገውን የደምወዝ ማሻሸያ ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።


 

በቅርቡ የሚከበረውን የዘመን መለወጫና ሌሎች የሚከበሩ በዓላት ላይም የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከክልሉና ከተጎራባች አካባቢዎች ምርት በስፋት እንዲቀርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ክልሉ ሰፊ የእንሰሳት ሃብት ያለበት በመሆኑ የእርድ እንስሳት እጥረት እንደያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፋብሪካና የግብርና ምርት የፍጆታ ዕቃዎች ጋር በተያያዘም በመንግስትና በንግዱ ማህበረሰብ በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ  እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለማህበረሰቡ ምርቶችን ተደራሽ ለማድረገም የአደባባይ የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎችን የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና ምርት ለመሰወር የሚሞክሩ አካላትን ለመቆጣጠርና እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባም ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም